የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት አራተኛው ሩብ ዓመት እንዲሁም በ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት አንደኛው እና ሁለተኛው ሩብ ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሉ ሁሉም ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎች እና በቀጠሮ እስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባከናወናቸው የክትትል ሥራዎች የተለዩ ግኝቶች ላይ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በባምባሲ ከተማ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የክልሉ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ የፍትሕ ቢሮ ተወካዮች፣ የአሶሳ፣ የካማሺ እና የመተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ ኢሰመኮ በክትትሉ የለያቸው መልካም እመርታዎች እና አሳሳቢ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከትርፍ ሰዓት ክፍያ ጋር ተያይዞ ተቋርጦ የቆየው የአዳር ሕክምና መቀጠል፣ በመተከል እና አሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች ይስተዋል የነበረው የንጹሕ ውሃ አቅርቦት እጥረት መሻሻል፣ የማረፊያ ክፍል መጣበብን ለመቅረፍ በመተከል ዞን ማረሚያ ቤት አዲስ ግንባታ ተከናውኖ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ፣ 40 ብር የነበረው የነፍስ ወከፍ የታራሚዎች የቀን በጀት ወደ 65 ብር ከፍ ማለቱን ተከትሎ የምግብ አቅርቦትና ስብጥር መሻሻሉ እንዲሁም ከወላጆቻቸው ጋር ማረሚያ ቤት የገቡ ሕፃናት የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት እንዲከታተሉ መደረጉ በማራሚያ ቤቶች ከታዩ መልካም እመርታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።


በሌላ በኩል በቅበላ ወቅት ልዩ ፍላጎትንና የአደገኛነት ሁኔታን ከግምት አለማስገባት፣ ከምግብ ዝግጅት ጋር የተያያዘ የጥራት ችግር መኖርና ከወላጆቻቸው ጋር ማረሚያ ቤት ለገቡ ሕፃናት በቂ የምግብ አቅርቦት አለመኖር፣ የመጸዳጃ ቤቶች እና የማደሪያ ክፍሎች ንጽሕና መጓደል፣ የተወሰኑ መድኃኒቶች እጥረት መኖር፣ የትምህርት ቁሳቁስ አለመሟላት፣ የቀጠሮ እስረኞች በቀጠሯቸው ቀን ፍርድ ቤት አለመቅረብ፣ እንዲሁም በሁሉም ማረሚያ ቤቶች ያሉ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ እና የአስተዳደር ሕንጻዎች አካል ጉዳተኛታራሚዎችን ልዩ ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ አለመሆን በውይይቱ ከቀረቡ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል የተለዩ ግኝቶች በተጨባጭ በማረሚያ ቤቶች ያሉ ችግሮችን ያሳየ መሆኑን ገልጸው የበጀት እና የተሽከርካሪ እጥረት መኖር፣ በመንግሥት በኩል ለክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ አናሳ መሆን እንዲሁም አስፈላጊ ግብአቶች አለመሟላት በማረሚያ ቤቶች ለሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል። የማረሚያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በማረሚያ ቤቶች የሚታዩ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ችግሮች እንዲሻሻሉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ተወካይ በዚህ ዓመት የአመክሮ ተጠቃሚ ታራሚዎችን ለይቶ ለውሳኔ ማቅረብ አለመቻሉ ተገቢ አለመሆኑን ጠቀሰው በቀጣይ የሦስቱ ሩብ ዓመት ተጠቃሎ ለውሳኔ እንደሚቀርብ እንዲሁም ብዛት ያላቸው ታራሚዎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ልዩ የይቅርታ መመሪያ ተዘጋጅቶ እንዲጸድቅ ለክልሉ መንግሥት መቅረቡን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች እና የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች መብቶች አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማሻሻል የትግበራ ዕቅድ በማዘጋጀት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና የታራሚዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብና የተቀናጀ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።