የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ወደቀድሞ ቀያቸው የተመለሱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ በክልሉ ከሚገኙ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ ተወያይቷል።
ውይይቱ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ተፈናቅለው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው ከቆዩ በኋላ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነትን ተከትሎ ጦርነቱ በመቆሙ ወደ ቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው ማለትም ወደ ኮረም ከተማ፤ ኦፍላ ወረዳ፣ ሕጉም ቡርዳ እና ፋላ ቀበሌ፤ ራያ አላማጣ ወረዳ፣ ዋጃ ጡሙጋ ቀበሌ፤ በአላማጣ ከተማ 02 እና 03 ቀበሌ እንዲሁም ጸለምት፣ ላዕላይ ጸለምት እና ማይፀብሪ ከተማ እንዲመለሱ የተደረጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለመረዳት እና ለማሻሻል ይረዳ ዘንድ ኢሰመኮ ከነሐሴ 19 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የለያቸው ግኝቶች እና የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ ያተኮረ ነው።
በውይይት መድረኩ ከጸጥታ እና ደኅነነት፣ ከመሠረታዊ አገልግሎት እና ከሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እዲሁም ከማኅበራዊ አገልግሎት አንጻር የተለዩ ግኝቶች ቀርበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ከተመለሱ በኃላ መሠረታዊ አገልግሎት እና የሰብአዊ ድጋፍ አለማግኘታቸውን እና በጸጥታ ሥጋት ምክንያት ተመላሾቹ ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ አሁንም ድረስ በትምህርት ቤቶች ተጠልለው ለመኖር ስለመገደዳቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም አስፈላጊ ማኅበራዊ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በፈረቃ ትምህርት መስጠት የተጀመረ ቢሆንም ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን፤ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማግኘት መቸገራቸውን እና ቅሬታ የሚያቀርቡበት አካል አለመኖሩን አንስተዋል።
ከአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኙ ተሳታፊዎች በመሠረታዊ አገልግሎት እና በሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እና በቀጣይ የምግብ አቅርቦቱን ለማሻሻል በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ጋር የሚሠሩ መሆኑን ገልጸዋል። ከትምህርት እና ከጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተገኙ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ የትምህርት እና የጤና ተቋማትን ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ፣ በቀጣይ የሚከናወኑ ተፈናቃዮችን ወደቀድሞ ቀያቸው የመመለስ ተግባር እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ የማድረግ ሂደት የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶችን መሠረት ያደረገ እና ያሟላ መሆኑ በቅድሚያ ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስረድተዋል።