የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ የሚገኙ ሕንጻዎች የተደራሽነት ሁኔታን በተመለከት ታኅሣሥ 17 እና 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ በሕንጻዎች የተደራሽነት ክፍተት ምክንያት የተለያዩ የመብት ጥሰቶች የደረሱባቸው አቤቱታ አቅራቢ አካል ጉዳተኞች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_161851_521-edited-1.jpg?resize=960%2C720&ssl=1)
በአቤቱታ መቀበያ መድረኩ ኢሰመኮ ከዊልቼር እና ክራንች ተጠቃሚ እግር ጉዳተኞች፣ ከዐይነ ስውራን እና መስማት ከተሳናቸው 15 አቤቱታ አቅራቢዎች ከ50 በላይ አቤቱታዎችን ተቀብሏል። አቤቱታዎቹ ከትምህርት፣ ከጤና እና ከሥራ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የባንክ አገልግሎት፣ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፣ በተለያዩ ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የግል ሕንጻዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው። አቤቱታ አቅራቢ አካል ጉዳተኞች የሕንጻዎች ተደራሽ አለመሆን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ እንቅፋት በመሆኑ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ እንዳገዳቸው ገልጸዋል።
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_165653.jpg?resize=960%2C960&ssl=1)
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_164358.jpg?resize=960%2C960&ssl=1)
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_161935_578-edited.jpg?resize=960%2C960&ssl=1)
አቤቱታው የቀረበባቸው ተቋማት እና በሕንጻ ግንባታ እና ቁጥጥር ረገድ ሕግ እና ፖሊሲ የማርቀቅ እንዲሁም አተገባበሩን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው የመንግሥት አካላትም የተነሱት ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የከተማ መሠረት ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን እና የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ፣ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ሕግ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ በመጥቀስ ከመድረኩ ያገኙትን ግብአት በመጠቀም በቀጣይ ለአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም መድረኩ የሕንጻዎች ተደራሽነት ጉድለት አካል ጉዳተኞች ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከዚህ ቀደም ባላስተዋሉት መጠን ለመረዳት ያስቻላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_164634.jpg?resize=1024%2C769&ssl=1)
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_164617.jpg?resize=1024%2C768&ssl=1)
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል በበኩላቸው በመድረኩ የቀረቡ አቤቱታዎች አስፈጻሚ አካላት ላይ ለሚያከናውኑት የቁጥጥር ሥራ ጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል። ሕንጻዎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በተለይም ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ሂደት የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚተጉ ገልጸዋል።
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/1000006382-edited.jpg?resize=960%2C720&ssl=1)
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2025/01/IMG_20250103_164237.jpg?resize=1024%2C768&ssl=1)
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በመድረኩ ቀርበው አቤቱታቸውን ያቀረቡ አካል ጉዳተኞችን ስለራሳቸው መብት መከበር ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር ለሚያደርጉት አስተዋጽዖ ዕውቅና ሰጥተው መድረኩ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ከማስፋፋት እና ከማረጋገጥ አንጻር ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።