የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ታኅሣሥ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትሎችና ምርመራዎች የደረሰባቸውን ግኝቶች በማቅረብ፣ መልካም እመርታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለመወትወት ያለመ ነው።

በውይይቱ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሃጂ አወል አርባን ጨምሮ የክልሉ አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊሰ ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም የሰላምና ጸጥታ ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ የትምህርት፣ ጤና፣ ባንክ እና መብራት አገልግሎቶች መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን የተዋቀረው የመልሶ ማቋቋም ጽሕፈት ቤት እንቅስቃሴ፣ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተደረጉ ጥረቶች፣ ሕግን ያልተከተለ እስር እንዳይኖር የተደረጉ ጥንቃቄዎች፣ ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ልምድ መሻሻሉ፣ በፖሊስ አባላት የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ለሚደርሱ ጉዳቶች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አመራሮች ቁርጠኝነት ማሳየታቸው፣ ለተጠርጣሪዎች የማደሪያ ክፍሎች፣ የመጠጥ እና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም የመጸዳጃ አገልግሎት መሻሻሉ እና የታራሚዎች ዕለታዊ የምግብ በጀት ከ50 ብር ወደ 100 ብር እንዲያድግ መደረጉ በመልካም እመርታነት ተገልጸዋል።

በሌላ በኩል በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤቶች ያለው የሕክምና፣ የምግብ፣ የአልጋ እና ፍራሽ አቅርቦት በቂ አለመሆን፣ የተጠርጣሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን ያልጠበቁና የአከባቢውን የአየር ሁኔታ ያላገናዘቡ እንዲሁም የታራሚዎች ክፍሎች የተጨናነቁ መሆናቸው በቂ ትኩረት እና ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።

ክቡር ሃጂ አወል አርባ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሃጂ አወል አርባ ኢሰመኮ ያቀረባቸውን ግኝቶች በበጎ እንደሚቀበሏቸው ገልጸው፣ የክልሉ መንግሥት ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ድክመቶችን ለማረም የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በሥራ ዕቅድና መርኃ ግብሮቹ ውስጥ አካቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል። በተለይም ክልሉ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገውን ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል እየሠራቸው ያሉ ተግባራትን ጠቅሰው፣ ኢሰመኮ በዚህ ድርጊት ሰለባ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳቶችን እና የባለድርሻ አካላት ኃላፊነቶችን በተመለከተ የግንዛቤ ማሳደጊያ ተግባራትን በማከናወን ጭምር ክልሉ በሚያደርገው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የማሻሻል ጥረት አስተዋጽዖ ማድረጉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ብርሃኑ አዴሎ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በክልሉ ያለውን ሰላም በማስቀጠል፣ የሰብአዊ መብቶች መርሖዎችንና ድንጋጌዎችን በተከተለ መልኩ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት ዕሴቶችን ከመደበኛው የፍትሕ አስተዳደር ጋር በማቀናጀት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው፤ ኢሰመኮ በክልሉ የሚያከናውናቸውን የግንዛቤ ማሳደግ፣ የክትትል እና የውትወታ ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።