የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እና የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ኢሰመኮን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 210/1992 አንቀጽ 15 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) መሠረት በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሦስት ወር ማስጠንቀቂያ አስቀድመው በጽሑፍ ማቅረባቸውን እና ምክር ቤቱም አሠራሩን ተከትሎ ጥያቄያቸውን መቀበሉን ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።
ራኬብ መሰለ በኢሰመኮ ከፍተኛ አማካሪነት የኮሚሽኑን ተቋማዊ ማሻሻያ እና መዋቅራዊ ለውጥ በኃላፊነት ከአንድ ዓመት በላይ ሲመሩ ከቆዩ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ልዩ ስብሰባ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ቀን ርግበ ገብረሐዋሪያ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር ኃላፊነትን ደርበው እያገለገሉ ቆይተዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንዲሁም ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በኢሰመኮ በነበራቸው ቆይታ በትጋት፣ በታማኝነት እና በቁርጠኝነት ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ አገልግለዋል።
ኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለን እና የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያን ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋና ያቀርባል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንዲሁም ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ ላለፉት ዓመታት ሕዝብን እና ኢሰመኮን ለማገልገል በእምነት ለተሰጣቸው ትልቅ ኃላፊነት ምስጋና አቅርበዋል።
የቀጣይ የአመራር ሽግግር ሂደት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ እና በኢሰመኮ የውስጥ አሠራር መመሪያዎች መሠረት የሚካሄድ ይሆናል። ኢሰመኮ እንደ ገለልተኛ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋምነቱ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን የመከታተል፣ የመመርመር፣ ሪፖርት የማድረግ እና የመደገፍ ሥራዎችን እንዲሁም በማቋቋሚያ አዋጁ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በሙሉ ቁርጠኝነት ማከናወኑን ይቀጥላል።