የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን በማሻሻል፣ በተለይም ከመጪው 7ኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ዐቅምና ዝግጁነት ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወያይቷል። ውይይቱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመረጃ ተደራሽነት መብቶችን በማረጋገጥ እንዲሁም በሰብአዊ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ተሳትፎን በማሳደግ ረገድ ሁለቱ ተቋማት በሚኖራቸው ሚና ላይ ለመምከር እና ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።


በውይይቱ ኢሰመኮ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተፈጻሚነትን አስመልክቶ ባከናወናቸው ክትትሎች የተለዩ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃን በሰብአዊ መብቶች መከበርና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና፣ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን፣ ሚዛናዊነትና አካታችነት ሁኔታ እንዲሁም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን እና ሰብአዊ መብቶችን አክብሮ በመንቀሳቀስ ረገድ የሚስተዋሉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በውይይቱ ተነስተዋል። ሁለቱ ተቋማት መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅት ንቁ፣ ነጻ እና ሚዛናዊ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያለሙ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠናዎችን ጨምሮ ሌሎች የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን እንዲሁም የኅብረተሰቡን መረጃ የማግኘት መብት በማረጋገጥ ረገድ በጋራ ሊያከናውኗቸው በሚችሏቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በዚህም ከሰብአዊ መብቶች ዘገባ ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን ለመስጠት፣ ክትትልና ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር እንዲሁም ግልጽ፣ ተጠያቂነት ያለው እና ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ የመገናኛ ብዙኃን ምኅዳርን ለመፍጠር መደበኛ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በጋራ እንደሚሠሩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳምሶን መኮንን በሰብአዊ መብቶችና በዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እና በኃላፊነት መሥራታቸውን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ንቁ እና ነጻ መገናኛ ብዙኃን ለሰብአዊ መብቶችና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢሰመኮ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ እንዲከናወን የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልጸዋል።