የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አፈጻጸምን የሚከታተል ነጻ የሆነ የክትትል ማዕቀፍ (Independent Monitoring Mechanism) በስምምነቱ አንቀጽ 33 (2) መሠረት መሰየም አስፈላጊነት ዙሪያ ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የሚደራጀው የክትትል ማዕቀፍ በስምምነቱ የተካተቱ መብቶችን ለማስፋፋት፣ ለመጠበቅ እና ለመከታተል ሊያከናውናቸው ከሚገቡ ቁልፍ ተግባራት መካከል ነባርና ረቂቅ ሕጎችን እንዲሁም ፖሊሲዎችን ከስምምነቱ መስፈርቶች ጋር ማጣጣም፤ ለመንግሥት አካላት የቴክኒክ ድጋፍና የዐቅም ግንባታ መስጠት፤ በጥቆማ ወይም በራሱ ተነሳሽነት ሪፖርቶችን ማውጣትና የመብት ጥሰት አቤቱታዎችን መመርመር ይገኙበታል። በተጨማሪም ጉዳዮችን ለፍርድ ቤት ማስተላለፍ፣ የሕግ አፈጻጸም መለኪያዎችን በማውጣት ተጽዕኖዎችን መገምገም እንዲሁም የስምምነቱ አተገባበር ላይ ያሉትን ልምዶች ያካተተ የመረጃ ቋት (data base) ግንባታ የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።የሚሰየመው ነጻ የሆነ የክትትል ማዕቀፍ በስምምነቱ አንቀጽ 33(1) መሰረት ከሚሰየሙት ስምምነቱን የማስፈጸም ተልዕኮ እንዲወጡ ከሚጠበቁት አካላት የተለየ እና ከአስፈጻሚው አካል ነጻ የሆነ ማዕቀፍ ነው። በዚህም መሠረት በሕግ አስፈጻሚው አካል ሥር የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አፈጻጸምን ከሚከታተለው አካል ጋር ያለውን ልዩነት፣ የአሰያየም ሂደት እና የሌሎች ሀገራት ልምድ ቀርቧል።

ኢሰመኮ የስምምነቱ ነጻ የሆነ የክትትል ማዕቀፍ እንዲያከናውናቸው የሚጠበቁ ሥልጣንና ተልዕኮዎች በመቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) ያሉት በመሆኑ ስምምነቱን የማስፋፋት፣ የመጠበቅ እና ከክትትል ጋር ተያያዥ የሆኑ ተግባራት በተለይም በአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች የሥራ ክፍል በኩል እየተፈጸሙ ይገኛሉ። በተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 33(2) መሠረት የሚሰየመው ነጻ የሆነ የክትትል ማዕቀፍ እንዲያሟላቸው የሚጠበቁ ተጨባጭ እና የተግባር ነጻነቶችን ኢሰመኮ ያሟላ እና በፓሪስ መርሖች መሠረት የ‘A’ ደረጃ እውቅና የተሰጠው በመሆኑ፤ አዲስ ተቋም ማደራጀት ሳያስፈልግ ኢሰመኮ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተል ነጻ የሆነ የክትትል ማዕቀፍ ሆኖ እንዲሰየም ያስችለዋል።

በውይይት መድረኩ የክትትል ማዕቀፉ የአሰያየም ዘዴዎች፣ አደረጃጀት፣ እንዲሁም ሥልጣንና ኃላፊነትን አስመልክቶ በስምምነቱ አንቀጽ 33(1) መሠረት የስምምነቱን አፈጻጸም እንዲከታተል በተሰየመው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአንቀጽ 33(2) መሠረት በነጻ ተከታታይነት እንዲሰየም በሚጠበቀው ማዕቀፍ መካከል ያለውን ተቋማዊ ሚና በግልጽ በመለየት የሥራ መደጋገምን ማስቀረት እንደሚገባ ተብራርቷል።  ይህ ማዕቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እና ሌሎች አጋር ተቋማትን በኮሚቴ አባልነት የሚያካትትበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ተሰጥቶታል።

የኢሰመኮ አካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ የመንግሥትን አፈጻጸም በገለልተኝነት የሚከታተል ነጻ አካል መኖር አንደኛው መንገድ በመሆኑ፤ ኢሰመኮ የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አፈጻጸምን በነጻነት የሚከታተል አካል ሆኖ መሰየም የስምምነቱን አተገባበር በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ በማቋቋሚያ አዋጁ የተሰጠውን ሰብአዊ መብቶችን የማስፋፋት፣ የመጠበቅ እና የመከታተል ሥልጣን እና ኃላፊነት እንዲወጣ ለማስቻል በውይይቱ የተደረሰበትን የጋራ መግባባት እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተፈጻሚ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።