የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በ22 ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ባካሄደው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ ከጨፌ ኦሮሚያ፣ ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ እና ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በምክክር መድረኩ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ የሚቀበሉ መሆናቸው፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተደራሽነት እና የታራሚዎች መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ማሻሻላቸው፤ ታራሚዎችን በአመክሮ የሚለቁበት ሁኔታ ሕግን የተከተለ መሆኑ፤ የድብደባ እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ድርጊቶች አለመኖራቸው እና ለታራሚዎች መለያ አልባሳትን ለማሟላት ጥረት ማድረጋችው አበረታች መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በቂ፣ ጥራት ያለው እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ችግር፣ የሕክምና አገልግሎት ውስንነት፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች እጥረት፣ የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ መሆናቸው፤ ታራሚዎችን በፈርጅ ለያይቶ በመያዝ ረገድ ክፍተት መኖሩ እንዲሁም ከወላጆቻቸው ጋር ለሚኖሩ ሕፃናት፣ ለነፍሰ-ጡር ሴቶች፣ ለሚያጠቡ እናቶች፣ ለአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ፍላጎቶቻቸውን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች አለመኖራቸው በአሳሳቢነት የቀጠሉ ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች የክትትሉ ግኝቶች በማረሚያ ቤቶቹ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው መንግሥት ለአንድ ታራሚ በቀን የሚመድበው 41 ብር ከ60 ሳንቲም በጀት ከወቅቱ የገበያ ዋጋ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ፤ ለምግብ ከተያዘው በጀት ላይ የመብራትና የውሃ ክፍያ የሚፈጸም መሆኑ እና የመብራት እና የውሃ ፍጆታ ላይ የታሪፍ ጭማሪ መደረጉ ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር መባባስ ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተው መፍትሔ ለማፈላለግ የሁሉም ባለድርሻዎች ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በውይይቱ ማጠቃለያም የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ለመፈጸም የሚረዳ የድርጊት መርኃ ግብር በኢሰመኮ እና በተሳታፊዎች በጋራ ተዘጋጅቷል።

የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኢጃራ ጋረደው በቀረቡ ምክረ ሐሳቦች መሠረት ችግሮችን በራስ ዐቅም ለመቅረፍ እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ አካላትን እገዛ የሚሹትን በትብብር ለማስተካከል ከክልሉ መንግሥት ሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት መፍትሔ ለማስገኘት እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር (በግራ) እና በዳሳ ለሜሳ፣ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ተጠባባቂ ከፍተኛ ዳይሬክተር (በቀኝ)

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ተጠባባቂ ከፍተኛ ዳይሬክተር በዳሳ ለሜሳ በማረሚያ ቤቶች እየታየ ያለውን መሻሻል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ እንዲሁም በአሳሳቢነት የቀጠሉ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አክለውም ኢሰመኮ የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩ የሚያደርገውን የግንዛቤ ማስፋፋት እና የውትወታ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።