የአትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 20 ማረሚያ ቤቶች ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በለያቸው ግኝቶች እና በ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና በሥሩ የሚገኙ 32 ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊዎችን ጨምሮ የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የጨፌ ኦሮሚያ፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ እና ሴንተር ፎር ጀስቲስ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ይበቃል ግዛው (በግራ) እና የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል (በቀኝ)

ኢሰመኮ ባቀረበው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት በታራሚዎች መረጃ አያያዝ፣  ታራሚዎችን በፈርጅ ለይቶ በመያዝ፣ የቀለም ትምህርት በማስተማር፣ በታራሚዎችና በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መካከል መልካም ግንኙነትን በመፍጠር፣ ድብደባ እና ተያያዥ ኢሰብአዊ  አያያዞችን በመቀነስ፣ ታራሚዎችን በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ በመቀበል፣ የማረሚያ ቤቶች ግቢ እና የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ንጽሕናን በመጠበቅ እንዲሁም የውሃ አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ አበረታች ግኝቶች መኖራቸው ተገልጿል። በተጨማሪም በማረሚያ ቤቶች የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ከክልል እስከ ወረዳ/ከተማ ቁልፍ ባለድርሻዎችን ያሰባሰበ ቦርድ መዋቀሩ በመልካም እመርታነት ተጠቅሷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በሌላ በኩል አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ለሴት ታራሚዎች የሚሰጡት የትምህርትና የሙያ ስልጠና እንዲሁም የሥራ ዕድል አነስተኛ መሆኑ፣ ለሴቶች የተመቻቸ የአምልኮ ስፍራ አለመኖሩ፣ የሴቶችን በተለይም የነፍሰጡሮችን ልዩ ፍላጎት ያማከለ የንጽሕና መጠበቂያና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች አለመቅረባቸው እና በዚህም ረገድ የሕግ ማዕቀፍ ክፍተት መኖሩ፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚቆዩ ሕፃናትን አያያዝ በሚመለከት ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እና የአሠራር ሥርዓት አለመዘርጋቱ እንዲሁም ለአእምሮ ሕሙማን እና ለአካል ጉዳተኛ ታራሚዎች ልዩ ፍላጎታቸውን ማእከል ያደረገ ድጋፍ አለመኖሩ መሻሻል የሚገባቸው ክፍተቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻፊ ሁሴን ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስረድተዋል። አያይዘውም ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች ክትትሉ የለያቸውን ክፍተቶች ዐቅም በፈቀደ መጠን ለማረም እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በክልሉ የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ አበረታች ለውጦች ቢኖሩም ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም በውይይቱ በተነሱ ክፍተቶችና ምክረ ሐሳቦች መሠረት በባለድርሻዎች የተዘጋጀው የምክረ ሐሳቦች ትግበራ ድርጊት መርኃ ግብር በአግባቡ ሊተገበር እንደሚገባ እና ኢሰመኮም ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡