የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዋና ዋና ተግባራት እና ኃላፊነቶቹ እንዲሁም ትኩረት በሚሹ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ዙሪያ ሐምሌ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች አባላት ጋር ሁለተኛ ዙር ስልጠና እና ውይይት አካሂዷል። የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና የኢሰመኮ ልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራ መሪዎች የተሳተፉበት የመጀመሪያው ዙር ሥልጠናዊ ውይይት ሰኔ 22 እና 23 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደ መሆኑ ይታወሳል።

ብርሃኑ አዴሎ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ስልጠና እና ውይይቱ ኢሰመኮ ከምክር ቤቱ ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማሳደግ፣ በአዋጅ በተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች ላይ ግልጽነት ለመፍጠር፣ እያከናወናቸው የሚገኙ ዋና ዋና ተግባራትን ማስገንዘብ እና ትኩረት በሚሹ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን በመፍጠር የምክር ቤቱን ቀጣይነት ያለው አዎንታዊ እገዛ ለማግኘት ያለመ ነው።

በመድረኩ በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ምንነት፣ በኢሰመኮ የሪፎርም ሥራዎች፣ የትኩረት መስኮች እና ተግዳሮቶች፣ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ፣ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ላይ የኢሰመኮ ሚና እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ በኢሰመኮ የተለያዩ የዘርፍ መብቶች የሥራ ክፍሎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የሚመለከት ገለጻ የቀረበ ሲሆን ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶችን ይበልጥ ለማስፋፋት እና ለማስጠበቅ ውጤታማ ሥራ ማከናወን በሚችልባቸው መንገዶች ላይ ከተሳታፊዎቹ ጋር ውይይት ተደርጓል።

በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (United Nations Human Rights Council – UNHRC) ለኢትዮጵያ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ምላሽ መስጠት፤ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች፤ በአካል ጉዳተኞች፣ በአረጋውያን፣ በሴቶች እና በሕፃናት መብቶች ላይ ኢሰመኮ በማከናወን ላይ የሚገኙ ሥራዎች፤ ትኩረት የሚፈልጉ የመብት ሁኔታዎች እንዲሁም ከእነዚህ አንጻር ምክር ቤቱ እና ኮሚሽኑ አብረው ሊሠሩ በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።

ተሳታፊዎች ስልጠናው ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ በመናበብና ይበልጥ በመተጋገዝ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ የኢሰመኮ ቁልፍ ተግባራት እና ኃላፊነቶች ላይ ግልጽነት እንዲፈጠር ዕድል የሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የኢሰመኮን ውጤታማነት ለማጎልበት ሊያደርግ የሚገባውን እገዛ ያስገነዘበ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ ኢሰመኮ ባለድርሻ አካላት የሰብአዊ መብቶችን እና ድንጋጌዎችን በበቂ ሁኔታ ተገንዘበው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ፤ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የመከላከል ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲያከናውን እንዲሁም ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ በመሥራት የሀገሪቱን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት ምክር ቤቱ የበኩሉን ድጋፍና ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል። ኢሰመኮ የሚሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦችን አጣርቶ እና ተከታትሎ ማስፈጸም እንዲሁም ለሥራ ግብአት የሚሆኑ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ ጥበቃ እና መከበር ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ከሆነው ምክር ቤት ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል። የስልጠና እና የውይይት መድረኩ ኢሰመኮ በቀጣይ ከምክር ቤቱ ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር እና የጋራ መግባባት የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።