“የአካል ጉዳተኞችን መሪነትና ተሳትፎ ለማረጋገጥ አካታች፣ ተደራሽ እና ዘላቂ ድኅረ ኮቪድ-19 ዓለምን እንገባ” የሚለው የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን መሪ ቃል በውስጡ በርካታ ጽንሰ ሃሳቦችንና ጥሪዎችን የሚያስተላልፍ ነው። ኮሚሽኑ ይህንኑ ቀን ለማሰብ ባሰራጨው በዚህ አጭር ቪድዮ የአካል ጉዳተኞችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካላት ከወዲሁ መወሰድ ስለሚችሉ እርምጃዎች ግንዛቤ ይሰጣል፣ ውትወታ ያደርጋል። ይህም ባለፉት ስድስት ወራትና በቀጣይነትም ኮሚሽኑ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ገደብ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቶ ክትትል ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች መካከል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መሰረተ ልማቶች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች የስራና የሌሎች እድሎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሏቸው ተቋማዊና ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና አሰራሮች እንዲዘረጉና እንዲሻሻሉ ግፊት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
አንድ አምስተኛው የዓለማችን ሕዝብ አካል ጉዳተኞች ቢሆኑም በተሳትፎም ሆነ በመብቶች ተጠቃሚነት አሁንም በርካታ መሰናክሎች የሚገጥሟቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ከብዙ ሀገራት ተሞክሮ እንዳየነው መንግሥታት ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አይነት ግዜ ለማለፍ ወይም ለመወጣት ሲሉ የእቅዶችንና የተግባራትን ቅደም ተከተሎች ይቀይራሉ፣ በጀት ያሸጋሽጋሉ። የአካል ጉዳተኞች፣ የሴቶችና ሕጻናት ወይም የአረጋውያን መብቶች ጉዳዮች በአብዛኛው በዚህ ሁኔታ ከሚሸጋሸጉ ብሎም ከሚታጠፉ ዘርፎች መካከል ናቸው። ሆኖም ግን በግጭት ወይም በጦርነት ወቅት፣ አልያም እንደ ድርቅ ባሉ ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ለጉዳትና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሚሆኑት እነዚሁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋዎቹ በሚያደርሱት ቀጥተኛና ተዛማች ጉዳቶች ምክንያት የአካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን ወይም ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት ቁጥር ሊጨምር ይችላል።
ስለሆነም በወቅታዊው የሀገር ሁኔታ የሚቀረጹ ወይም የሚከለሱ እቅዶች ለእነዚህ ማኅበረሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት የሚሰጡና ያማከሉ ሊሆኑ ይገባል። በተለይም በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን መልሶ ለማቋቋምና ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችና የሚቀረጹ እቅዶች አካል ጉዳተኞችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉና ለሁሉም ማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባለ።
ራኬብ መሰለ
ምክትል ዋና ኮሚሽነር
ብሌን ገብረመድኅን
ዳይሬክተር
የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች የስራ ክፍል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)