የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከፍሬድሪክ ኤልበርት ስቲፍታንግ (Friedrich Elbert Stiftung) ጋር በመተባበር የንግድ እና የሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር ዝግጅት ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። በመርኃ ግብሩ የመንግሥት ከፍተኛና መካከለኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማ የልማትና የእድገት እንቅስቃሴዎች ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ እንዲመሩ ሊወሰዱ በሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ መምከር እና የንግድና የሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር ዝግጅትን ማስጀመር ነው፡፡
በብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር ዝግጅት ማስጀመሪያ መድረኩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የሰብአዊ መብቶች መርሖች እና ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎች(International trends)፣ ተቋማት የንግድና የሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር በመንደፍ ሂደት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚናና ሊከተሏቸው የሚገቡ ሂደቶች እንዲሁም የንግድና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚመለከቱ የውይይት መነሻ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ ከዳኒሽ የሰብአዊ መብቶች ተቋም (Danish Institute for Human Rights) ጋር በመተባበር ወደ አማርኛ ቋንቋ የተረጎመው የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖችን (United Nations Guiding Principles on Business and Human Rights) የያዘ ሰነድ በዕለቱ ይፋ ተደርጓል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የድርጊት መርኃ ግብሩን የማዘጋጀት ሥራውን እየመራ የማስተባበር ሚናውን እንደሚወጣ በመግለጽ፣ የድርጊት መርኃ ግብሩን ለማዘጋጀት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የማድረግ ተቀዳሚ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን ጠቅሰው ኢሰመኮ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ውትውታ፣ ምክክር፣ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትሎችንና ምርመራዎችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰዋል። አክለውም ኢሰመኮ በአከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ግኝቶች የንግድ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነታቸውን ሙሉ በሙሉ ከመወጣት አንጻር በርካታ ክፍተቶች የሚስተዋሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን ክፍተቶች ለመቅረፍና የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ የንግድ እና የሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር መዘጋጀት አስፈላጊነትን ገልጸዋል።