የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በልዩ አዳሪ እና ቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ አራተኛ ዙር ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ አካሂዷል። በውይይት መድረኩ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ ክትትል የተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች፣ መንግሥታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ኢሰመኮ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ሰብአዊ መብቶችን አስመልክቶ በአዲስ አበባ፣ አምቦ፣ ባሕር ዳር፣ ቢሾፍቱ፣ ባኮ፣ ጋምቤላ፣ ሆሳዕና፣ መቐለ፣ ሰበታ እና ሻሸመኔ ከተሞች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ያካሄደ ሲሆን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዙር የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እንዲሁም ሦስተኛውን ዙር በሃዋሳ ከተማ ማካሄዱ ይታወቃል።

በቀረበው የክትትል ሪፖርት በክልሉ ያለው ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት፣ የትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ አለመሆን እና የተደራሽነት ውስንነት፣ በአካቶ ትምህርት ቤቶች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖር፣ በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸው፣ በጦርነቱ አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተማሪዎች ለማስተናገድ በቂ የሆነ በጀት አለመኖር ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸው ተጠቅሷል። በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች በጦርነት ምክንያት የተለያዩ የአካል ጉዳቶችን በተለይ ተደራራቢ ጉዳት የደረሰባቸውን ተማሪዎች ለማስተናገድ ያለባቸው የበጀት እንዲሁም የሰው ኃይል ውስንነት፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶች በሚመለከተው የመንግሥት አካል በቂ ትኩረት አለማገኝት አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።

በመድረኩ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች የጉዳት ዓይነታቸውን የሚመጥን ሥርዓተ ትምህርት ባለመኖሩ በትምህርታቸው እንዳይገፉ እና ውጤታማ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ማነቆ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በኢሰመኮ የቀረቡ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦችን በትብብር ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የኢሰመኮ የክትትል ሥራ ግኝቶች በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ በሚገባ የሚያሳዩ መሆናቸውን በመጥቀስ የሚመለከታቸው የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ርግበ ገብረሐዋርያ፣ የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከጉዳት አልባ አቻዎቻቸው እኩል በትምህርት ውጤታማ እንዳይሆኑ ከባቢያዊ፣ ተቋማዊ እንዲሁም ከአመለካከት እና ከመረጃ እና ተግባቦት ተደራሽነት ጋር የተያያዙ መሰናክሎች እንደሚገጥሟቸው ገልጸዋል አክለውም “በግጭት ዐውድ ውስጥ የቆዩ ቦታዎች/ ክልሎች የሚኖሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ለተደራራቢ እና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች በጋራ መፍታት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።