የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዓለም አቀፉን የአካል ጉዳተኞች ቀን ለማሰብ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሃዋሳ ከተማ ባዘጋጁት መርኃ ግብር ላይ ተሳትፏል። በመርኃ ግብሩ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች አንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት መሪዎችና አባላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ ኢሰመኮ ከሦስት ዓመታት በፊት ተቋማዊ ለውጥ ባካሄደበት ወቅት ትኩረት ካደረገባቸው የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች አንዱ የአካል ጉዳተኞች መብቶች መሆኑ፤ የአካል ጉዳተኞች መብቶች በመንግሥት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲከበሩ እና እንዲጠበቁ ለማስቻል በሚያደርጋቸው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትሎችንና ምርመራዎች ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት እና ለተግባራዊነታቸውም ውትወታ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በሀገራችን በአካል ጉዳተኞች መብቶች ዙሪያ የታዩ አወንታዊ ለውጦች እና አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ተነስተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና ለማጉላት መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተወስኑ አካል ጉዳተኞችን ከማሳተፍ ባሻገር የጾታ እኩልነትን ጨምሮ የአካል ጉዳተኞችን ብዝኃነት በሚወክል መልኩ ድምፃቸውን ማጉላት እንዲሁም መብቶቻቸው እንዲከበሩ መትጋት እንዳለባቸው በመርኃ ግብሩ ተመላክቷል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ “የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት እና መብቶች በትክክል የሚያካትቱ እና የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችን እና የአሠራር ስልቶችን በማዘጋጀት አካል ጉዳተኞች ወደ መሪነት የሚመጡበትን ሁኔታ እና ተነሳሽነታቸውን ይበልጥ የሚያሳድጉበትን ከባቢ መፍጠር ይኖርብናል” ብለዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ሲከበር ኢትዮጵያ የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ እንደሚኖራት ያላቸውን ሙሉ እምነትም ገልጸዋል። የሲዳማ ክልል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን የአመራር ተሳትፎ ለማሳደግ ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ መንግሥት በረቂቅ ደረጃ ያለውን የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ እንዲጸድቅ ማድረግን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር የሚያግዙ ሁለንተናዊ የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ እና እንዲተገበሩ እንዲያደርግ ያሳሰቡ ሲሆን፣ አካል ጉዳተኞችም ይህ እንዲሆን የሚያደርጉትን ትግል በቅንጅት እንዲያጠናክሩና ውትወታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞች ሐሳባቸውን የሚያካፍሉበት እና በሚመለከቷቸው ሕጎች እና ፖሊሲዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉበትን መድረኮች ትርጉም ባለው መልኩ የማመቻቸት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡