የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የዳኝነት ነጻነት እና የፍትሕ አካላት ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ያላቸውን ሚና እንዲሁም የሽግግር ፍትሕን የተመለከተ ስልጠና ከሰኔ 15 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ እና ሚዛን አማን ከተሞች ሰጥቷል። በስልጠናው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ዳኞች፣ የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እንዲሁም የተለያዩ የፍትሕ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በስልጠናው በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ መከበር እና መስፋፋት ረገድ የፍርድ ቤቶች ሚና፣ የዳኝነት ነጻነት፣ የዳኞች ያለመከሰስ መብት የሕግ ማዕቀፍ፣ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና የባለግዴታዎች ምላሽ አሰጣጥ እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የተሞከሩ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችና የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን ጨምሮ የክልሎችና የፍትሕ አካላት ሚና ላይ ሰፊ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በስልጠናው በተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይት እንዲያደርጉ እድል የሰጠ በመሆኑ በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲይዙ እንደረዳቸው ገልጸው ተመሳሳይ ስልጠናዎች እና ትብብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወንዴ ኩርታ ኢሰመኮ በተለያዩ መንገዶች ከክልሉ ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ ሥራ ላይ በማዋል ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆነበት ክልል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ በበኩላቸው በክልሉ ያለው የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝና የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራዎች ትኩረት እንደሚሹ አስገንዝበዋል። አክለውም ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል የሚረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እንዲሁም የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።