የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በምርጫ ለመወዳደር የሚቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚያስገድደው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ድንጋጌ ለ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ተፈጻሚ እንዳይሆን ማገዱን በበጎ ይመለከተዋል።

ኢሰመኮ ባደረጋቸው ክትትሎች እንደተገነዘበው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩን በመጥቀስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ከዚህ ግዴታ ተፈጻሚነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በዚሁ መሠረት ምክር ቤቱ ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚያስገድደው ድንጋጌ ተፈጻሚነት ለ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲታገድ በመወሰን፣ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል። የምክር ቤቱ እርምጃ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ፣ በምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ እንዲሁም ምርጫው አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የምርጫ እና በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብቶችን ለማጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው።

በመሆኑም ኢሰመኮ ይህንን እርምጃ በበጎ መልኩ የሚመለከተው መሆኑን እየገለጸ፣ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልጽ፣ ተአማኒነት ያለውና ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የተከበሩበት እንዲሆን ለማድረግ የሚረዱ አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የማጠናከር ጥረቶች እንዲቀጥሉ መንግሥትን ጨምሮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪውን ያቀርባል።