የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳቶችን፣ የንብረት ጉዳት እና ዘረፋዎችን በተመለከተ ከሰኔ 20 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ያደረገውን ምርመራ ባለ 13 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በዚህ የምርመራ ሂደት ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከዓይን እማኞች እና ሌሎች ምስክሮች ጋር ቃለ መጠይቅ የተደረገ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 58 ሰዎችን (25 ሴቶች እና 33 ወንዶችን) አነጋግሯል። ኮሚሽኑ ከፍትሕ እና የጸጥታ ተቋማት ኃላፊዎች እና ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይቶች እና ቃለ መጠይቆችን አድርጓል። ለምርመራው ሥራ አግባብነት ያላቸውን የሰነድ፣ የፎቶ ግራፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ዲጂታል ማስረጃዎችን ሰብስቧል፤ እንዲሁም የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡
ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ታጣቂዎች በጋራ በመሆን ወደ ጋምቤላ ከተማ በመግባት ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ፤ ከክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ መደበኛ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ፌዴራል ፖሊስ ጋር ውጊያ ከተደረገ በኋላ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተማውን መልሰው መቆጣጠራቸው ይታወሳል፡፡
ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት በኋላ እንዲሁም ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሣሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሣሪያ አውጡ” በሚል ምክንያት ሴቶችና የአእምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን፣ ቢያንስ 25 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ላይ የመደብደብና የማሰቃየት ተግባር መፈጸሙን ኮሚሽኑ አረጋግጧል። በተጨማሪም በኦነግ ሸኔ፣ በጋነግ፣ በክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች በበርካታ ሰዎች ላይ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሟል።
ውጊያው በተካሄደበት በሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. የኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ታጣቂዎችም በተኩስ ልውውጡ ወቅት “ተኩሳችሁብናል” በሚል ምክንያት እና በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኟቸውን ቢያንስ 7 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ እንዲሁም በሲቪል ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ በበርካታ ሲቪል ሰዎችም ላይ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት አድርሰዋል፡፡ በተጨማሪም በተኩስ ልውውጥ ወቅት በየትኛው አካል እንደተገደሉ ያልታወቀ 6 ሰዎች ሞተዋል።
ኮሚሽኑ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከነዋሪዎች እና ከዓይን እማኞች በሰበሰበው መረጃ እና በሌሎች ማስረጃዎች በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲቪል ሰዎች አስክሬን በክልሉ ልዩ ኃይሎች እና መደበኛ ፖሊሶች በጭነት መኪና ተሰብስቦ ወዳልታወቀ ቦታ እንደተወሰደና በጅምላ እንዲቀበሩ የተደረገ መሆኑን፤ እንዲሁም አስክሬን እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ የሟች ቤተሰቦችም መከልከላቸውን አረጋግጧል፡፡
ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከደረሱት ግድያዎች፣ አካል ጉዳቶች፣ ንብረት ዘረፋ እና ውድመት በተጨማሪ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ለሥነልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፤ በርካታ ቤተሰቦችም ያለ ደጋፊ እንዲቀሩ ሆኗል፡፡
የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናት በተለያየ ወቅት ግጭቱን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው መግለጫዎች በአንድ በኩል “ወደ ከተማው የገቡት የኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ታጣቂዎች የሲቪል ሰዎችን ልብስ ጨምሮ የተለያዩ በሥራ ላይ ያሉ እና የሌሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችን መለዮ ልብሶች ለብሰው የነበረ በመሆኑ እና ውጊያው በከተማ ውስጥ በመከናወኑ የተለያዩ ብሔሮች ተወላጅ የሆኑ አስራ ሰባት (17) ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን” ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራር ከነበረው ውጊያ በኋላ በተደረገ የክልሉ መንግሥት አመራሮች ስብሰባ ላይ “እያንዳንዱ ስድስት እና ሰባት ሰው እየያዘ ወደ ዝርፊያ ነው የገባው” ሲሉ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር ኮሚሽኑ ተመልክቷል። በጋምቤላ ክልል መንግሥት የኮምኒኬሽን ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይም “ቁጥሩ በትክክል አይታወቅ እንጂ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚገልጽ” ጽሑፍ አውጥቷል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም 5 ሲቪል ሰዎች በውጊያው ወቅት በኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. መገደላቸውን፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎች 2 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ በየመንገዱ የነበሩ አስክሬኖች በከተማው ማዘጋጃ ቤት ተሰብስበው መቀበራቸውን፣ ዝርፊያ የተፈጸመ ስለመሆኑ የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉት ነገር ግን ጥሰቶቹ የተፈጸሙበትን ሁኔታ እና የፈጻሚዎችን ማንነት በተመለከተ የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ ለኢሰመኮ ገልጿል፡፡
የሟቾች አስክሬን ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተሰጠና የተቀበሩበት ቦታ ለምን ለቤተሰቦች እንዳልተገለጸ ኢሰመኮ ላቀረበው ጥያቄ የክልሉ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ አስክሬን ይሰጠን ብሎ ለፖሊስ ኮሚሽን ያመለከተ የከተማው ነዋሪ አለመኖሩን የገለጸ ሲሆን፤ በአንጻሩ ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበለት የከተማው ማዘጋጃ ቤት “ፊዴራል ፖሊስን አነጋግሩ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። የፌዴራል ፖሊስ በበኩሉ አስክሬኖች ተሰብስበው የተቀበሩት በማዘጋጃ ቤት መሆኑን ገልጿል።
የክልሉ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በበኩሉ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ጉዳዩን በተመለከተ የተባሉት ነገሮች “በአብዛኛው ውሸት ቢሆኑም አንዳንድ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሱ (ጉዳቶች) እንዳሉ” ይህንንም ያደረሱ የሥነ-ምግባር ግድፈት ያለባቸውን የክልሉን ጸጥታ ኃይሎች አጣርተው እርምጃ እንደሚወስዱ እና አንድ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ከውጊያው በኋላ ባደረገው ማጣራት የክልሉ ልዩ ኃይሎች በተለይ ሰኔ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማው በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ መረዳታቸውን እና መወሰድ ያለባቸውን ሕጋዊ እርምጃዎች መጠቆማቸውን ገልጸዋል።
ስለሆነም ኢሰመኮ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕ እና ተገቢውን የካሳ እና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል እንዲረዳ ያከናወነው ምርመራ፣ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች በዚህ ሪፖርት እያቀረበ፤ ተፈጻሚነቱን የሚከታተል መሆኑንም ያሳስባል።