የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል ከሚካሄደው የትጥቅ ግጭት ጋር ተያይዞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የነበረው እና ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተጨማሪ 4 ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ተፈጻሚነት ማብቃቱን ተከትሎ በእስር የቆዩ ሰዎችን የመልቀቅ ሂደት እንዲቀጥል ያሳስባል።

ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ከአዋጁ ትግበራ ጋር የተስተዋሉ ክፍተቶችንና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያመላክቱ፣ እንዲሁም ምክረ ሐሳቦችን ያካተቱ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውን ጋዜጣዊ መግለጫ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የክትትልና የምርመራ ሪፖርቶች ይፋ ሲያደርግ የቆየ መሆኑ ይታወሳል። በዚሁ አዋጅ አተገባበር ዐውድ ውስጥ በእስር ላይ የቆዩ ሰዎች እንዲለቀቁ ማድረግን ጨምሮ ወደ መደበኛው የሕግ አተገባበር ሂደት መመለስ፣ እንዲሁም በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ እና ሌሎች ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ ኢሰመኮ አክሎ ጥሪ ያቀርባል።