በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳል። በፌስቲቫሉ ለሕዝብ ዕይታ የሚቀርቡ የሥዕልና የፎቶግራፍ እንዲሁም የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውድድር ተዘጋጅቷል። ውድድሩ በ2016 ዓ.ም. በኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አሳሳቢ ተብለው ከተለዩ መብቶች መካከል በሕይወት የመኖር መብት አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ሆኖ በመቀጠሉ፣ በዘንድሮ ዙር በተለይም በሴቶች ሕይወት ላይ በማተኮር፣ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ዘርፍ ደግሞ በበቂ ምግብና ውሃ በማግኘት መብት ላይ በማተኮር ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሯል። ውድድሩ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በአርባምንጭ፣ በአሶሳ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ፣ በጋምቤላ፣ በጅግጅጋ፣ በጅማ፣ በመቀሌ እና በሰመራ ከተሞች እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ ዓመታዊ ፌስቲቫል ዓላማ ስለ ሰብአዊ መብቶች በኪነ ጥበብም ሆነ በሌሎች ሥራዎቻቸው የሚያወሱ እና የሚያበረታቱ ሰዎችን፣ ተቋማትን እና ድምፆችን ማሰባሰብ ነው። በተጨማሪም ፌስቲቫሉ ሰዎችን በአንድ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ዙሪያ በማስተባበር በሰብአዊ መብቶች ላይ ግንዛቤ ማሳደግ እና በኪነ ጥበብ አማካኝነት ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
በ2016 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ከፊልም ሥራዎች በተጨማሪ በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለተሰማሩ ጀማሪ እና ልምድ ላላቸው ሰዎች ዕድል ለመስጠት፣ ለማበረታታት እና ለሰብአዊ መብቶች ሥራዎች ድምፅ ለመሆን በማለም የአጫጭር ፊልም እና የፎቶግራፍ ውድድርን አካቶ ከ160 በላይ ሰዎች የኪነ ጥበብ ሥራቸውን ለኢሰመኮ በመላክ ተወዳድረዋል።
ኢሰመኮ በዘንድሮው 4ኛ ዙር ፌስቲቫል ውድድር የሚካሄድባቸውን የኪነ ጥበብ ዘርፎች በማስፋት፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዘት ጥራት ለማሳደግ የሚረዱ ውድድሮችና መሰል አሳታፊ ዝግጅቶችን በማካተት፣ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን እንዲሁም ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ብዛት በመጨመር የፎቶግራፍ፣ የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እና የሥዕል ውድድሮችን ያካሂዳል።
የሥዕልና የፎቶግራፍ ውድድሩ ትኩረቱን በቂ ምግብና ውሃ በማግኘት መብቶች ላይ ሲያደርግ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውድድር ደግሞ በሕይወት የመኖር መብት በተለይም በሴቶች ሕይወት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በአጫጭር የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ዘርፍ ለውድድር የሚቀርብ ሥራ ከ 3 ገጽ ያልበለጠ (ከ600 ቃላት ያላነሰ፣ ከ1200 ቃላት ያልበለጠ) ሊሆን ይገባል። በሁለቱም ዘርፎች የሚቀርቡ የጥበብ ሥራዎች ዘጋቢ፣ ምናባዊ ወይም እውነተኛ ታሪክ ላይ መሠረት ያደረጉ ሊሆኑ ይችላሉ።
ፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ለውድድር የተመረጡት የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች መከበር ወይም መጣስ በሰዎች ሕይወት ላይ ያለውን አንድምታ የሚገልጹ፣ የተለያዩ ሐሳቦችን የሚሰጡ፣ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን የሚያቀርቡበት ይሆናል። ለውድድር የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማለትም ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወይም ስደተኞችን ማእከል እንዲያደርጉ ይጠበቃል።
ውድድሩ የሚካሄድባቸው ከተማዎችና የውድድር ዘርፎች ከዚህ በታች ተገልጸዋል።
ተ.ቁ | ከተማ | የውድድር ዘርፍ | ውድድሩ የሚያተኩርበት ጭብጥ |
1. | አዲስ አበባ | የፎቶግራፍ እና የሥነ ጽሑፍ ውድድር | የሴቶች ሕይወት እና በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
2. | አዳማ | የፎቶግራፍ ውድድር | በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
3. | አርባምንጭ | የፎቶግራፍ ውድድር | በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
4. | አሶሳ | የሥዕል ውድድር | የሴቶች ሕይወት |
5. | ባሕር ዳር | የሥዕል ውድድር | የሴቶች ሕይወት |
6. | ሃዋሳ | የፎቶግራፍ ውድድር | በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
7. | ጋምቤላ | የሥዕል ውድድር | የሴቶች ሕይወት |
8. | ጅግጅጋ | የፎቶግራፍ ውድድር | በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
9. | ጅማ | የፎቶግራፍ ውድድር | በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
10. | መቀሌ | የሥዕል ውድድር | የሴቶች ሕይወት |
11. | ሰመራ | የሥዕል ውድድር | በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች |
ውድድሮቹ በሚካሄድባቸው ከተሞች የሚገኙ ፍላጎት ያላቸው ጀማሪም ሆኑ ልምድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ በውድድሮቹ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል። በተጨማሪም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ወይም የስልጠናና ትምህርት ሰጪ ተቋማት በውድድሩ መሳተፍ ይችላሉ።
በሁሉም የኪነ ጥበብ ዘርፎች በውድድሩ ለሚሳተፉ ግለሰቦች እና ተቋማት በሙሉ የዕውቅና ሰርተፊኬት የሚሰጥ ሲሆን፣ በተጨማሪም አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ሽልማት ተዘጋጅቷል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ታኅሣሥ 1 ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን ታሳቢ በማድረግ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቁመው፣ “ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል በጥበብ ሥራዎች ለሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ድምፅ ለመሆን እና ‘ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን’ ማየት የሚለውን የኢሰመኮን ራዕይ ለማሳካት በጋራ የምንሰባሰብበት ነው” ብለዋል። አክለውም በውድድሩ በተለይም ወጣቶች እና ታዳጊዎች እንዲሁም የኪነ ጥበብ ዘርፍ ባለሙያዎችና ለዚህ ራዕይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ስለ ፌስቲቫሉ እና ውድድሩ ተጨማሪ ዝርዝር እና የተሟላ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል
የውድድሮቹ የተሳትፎ ቅጽ፣ አጠቃላይ መመሪያዎች እና ደንቦች