የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ወር 2018 ዓ.ም. ባሉት 3 ወራት በሰብአዊ መብቶች፣ በሽግግር ፍትሕ፣ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች መብቶች አያያዝ እና በአረጋውያን መብቶች ብሎም በሰብአዊ መብቶች ተኮር አሠራር ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን በተለያዩ የክልል ከተሞች ለሚገኙ የወጣቶች ማኅበራት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ለፖሊስ አባላት ሰጥቷል።



ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ ያለመ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና ከተለያዩ የወጣት ማኅበራት ለተውጣጡ 67 ወጣት አመራሮች እና አባላት ከጥቅምት 24 እስከ 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰመራ እና በአርባምንጭ ከተሞች ሰጥቷል። በሌላ በኩል ኢሰመኮ ከዚሀ ቀደም በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የወጣቶች ሚናን በተመለከተ የአሰልጣኞች ስልጠና የሰጣቸው የወጣት ማኅበራት በዲላ ከተማ ከ5 ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ወጣቶች፣ ለሃይማኖት ተቋማት ወጣት ተወካዮች፣ እና ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ለተወከሉ ወጣት ማኅበራት በአጠቃላይ 49 ለሚሆኑ ተሳታፊዎች መልሰው ስልጠናውን እንዲሰጡ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ስልጠናዎቹ የሌሎች ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች የቀረቡበትና የወጣቶችን ጉልህ ሚና ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራዊ ልምምዶች የተካተቱበት ነው። በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ፅንሰ-ሐሳቦች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበትና በኢትዮጵያ ሊተገበር በታቀደው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ማስገንዘብ ተችሏል።



በሌላ በኩል ኢሰመኮ የወጣቶችን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በማዳበር ለሰላም፤ መከባበር እና መቻቻል ያላቸውን አስተዋጾ ለማሳደግ ያለመ ስልጠና ከምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ከነቀምት ከተማ እና አከባቢው ለተውጣጡ የወጣት ማኅበራት እንዲሁም ከአሶሳ እና አከባቢው ለተውጣጡ የወጣት ማኅበር አባላት ከጥቅምት 17 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በነቀምት እና አሶሳ ከተሞች ሰጥቷል፡፡ በእነዚህ ስልጠናዎች ወጣቶች ለሰላም፣ ለመቻቻል እና ለአብሮነት ያላቸውን ፍላጎት እንዲያሳድጉ እና ሰብአዊ መብቶች ለእነዚህ ቁልፍ የማኅበረሰብ ዕሴቶች ያላቸውን ሚና እንዲገነዘቡ አስተዋጽዖ ማበርከት ችሏል፡፡
በተመሳሳይ ኢሰመኮ ታዳጊ ተማሪዎች ስለመሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች ያላቸውን ዕውቀት እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ያላቸውን ተነሳሽነት በማጎልበት የሰብአዊ መብቶች ክበባትን ለማጠናከር ያለመ ስልጠና በአዲስ አበባ ሰጥቷል። ከታኅሣሥ 25 እስከ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. በተሰጠው በዚህ ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 8 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 32 የክበብ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም አስተባባሪ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡



ኢሰመኮ ባለፉት 3 ወራት በተለያዩ አገልግሎቶች አሰጣጥ እና የልማት ሥራዎች ወቅት የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እና ሰብአዊ መብቶች ተኮር አሠራሮችን ለማጎልበት ይቻል ዘንድ በድሬዳዋ ከተማ እና አካባቢዋ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበራት ከኅዳር 15 እስከ19 ቀን 2018 ዓ.ም. በድሬደዋ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው የተሳተፉ የሲቪል ማኅበራት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በሚነድፉበት ወቅት ታሳቢ ሊያደርጉዋቸው የሚገቡ የሰብአዊ መብት መርሖዎች ላይ ዕውቀታቸውን እና አመለካከታቸውን የሚያሳድግ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡ በተያያዘም ኢሰመኮ የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም መብቶቹን ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ክህሎቶችን ያካተተ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና ለአረጋውያን ማኅበራት አባላት እና አመራሮች ከኅዳር 1 እስከ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ የሰጠ ሲሆን ተሳታፊዎች አረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እና አቤቱታ ለማቅረብ እንዲሁም ውትወታ ለማድረግ የሚያስችሏቸውን ክህሎቶች ለማዳበር እንዲችሉ ተግባራዊ ልምምድ አድርገዋል።



በተጨማሪም ኢሰመኮ ባለፉት 3 ወራት የፖሊስ አባላትን እና አመራሮችን ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ዐቅምን ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና በቢሾፍቱ እና በጅማ ከተሞች ሰጥቷል። በጅማ በተካሄደው ስልጠና ከጅማ ዞን እና ከጅማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያዎች እንዲሁም በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው ስልጠና ላይ ከአዲስ አበባ 5 ክፍለ ከተሞች የተውጣጡና በወንጀል መከላከልና ምርመራ ዘርፍ የተሰማሩ የፖሊስ አባላት እና የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በስልጠናው ተሳታፊዎች መሠረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶችን በተለይም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ አድሎ አለመፈጸም እና ኃላፊነት ከፖሊስ ሥራ ጋር ስላላቸው ትስስር ግንዛቤ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ስልጠናው የተጠረጠሩና የተያዙ ሰዎች በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች መሠረት ስላሏቸው መብቶች እንዲሁም በኃይል አጠቃቀም መርሖዎች ላይ የተሳታፊዎችን ዕውቀትና አመለካከት ለማሳደግ የሚረዳ ነው።