የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ሁኔታ በመከታተል ላይ ይገኛል። 

ኮሚሽኑ ከኅዳር 5 እስከ ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በማይካድራ ተዘዋውሮ ምርመራ ካደረገ ብኋላ፣ ለሁለተኛ ዙር የመስክ ምልከታ ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013  ዓ.ም. ወደ ትግራይ እና አማራ ክልሎች ተጉዟል። በወቅቱ በተለይም በትግራይ ክልል የነበረው የፀጥታ ሁኔታ በክትትሉ እቅድ መሰረት ኮሚሽኑ ሊያካትታቸው ያሰባቸው አካባቢዎችን በሙሉ (ሁመራ፣ ማይካድራ፣ ዲማ፣ አዲ ጎሹ፣ ራውያን እና በረኧት) ለማካተት ባይችልም በጎንደር እና በዳንሻ በመገኘት በተለይም ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ተመልክቷል። እንዲሁም የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላትና ኃላፊዎች ከማነጋገር በተጨማሪ በሆስፒታል እና በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን፣ ተጎጂዎችን፣ በግጭቱ የተሳተፉ ሰዎችንና የህክምና ባለሞያዎችን አነጋግሮ መረጃ ሰብስቧል። 

ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ዞን፣ ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋ እና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ ከኅዳር 5 እስከ ኅዳር 8 ቀን 2013  ዓ.ም. ድረስ በአካባቢው ስለደረሰ የሲቪል ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት መድረስ እና የንብረት መዘረፍና መውደም ማጣራት አድርጓል። በተጠቀሱት ቦታዎች በመዘዋወር ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ምስክሮችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል። 

የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ዙር የመስክ ምልከታ ወደ መቀሌ ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብአዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ስራው እንደተጠናቀቀ ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ የሚደረግ መሆኑን እንገልጻለን።