Amhara region

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። 

ከሰኔ 21 ቀን እስከ ነሃሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው ይህ ሪፖርት እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደ ምርመራ ውጤት ሲሆን፣ የምርመራ ቡድኑ 128 ቃለመጠይቆችን፣  ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው፣  ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሲቪል እና የፀጥታ አካላት፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣  ከተራድዖ ድርጅቶች  ጨምሮ 21 የቡድን ውይይቶችን አድርጓል።  

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንዳመላከተው ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት  ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ እንዲሁም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተለይ የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ሆን ብለው መፈፀማቸውን አረጋግጧል። 

እንዲሁም የሕወሓት ኃይሎች ወደ ከተሞች ከባድ መሳሪያዎችን መተኮሳቸውን፤ በሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ምሽግ በመቆፈር እና ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ሲቪል ዜጎችን በአፀፋ ለሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ጥቃት ማጋለጣቸውን፤ በዚህም የበርካታ ሲቪል ሰዎች ሞት እና አካል ጉዳት እንዲከሰት እንዲሁም ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል። 

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት የሕወሓት ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈፅሙበትን ጥቃት ለመከላከል እና ለማጥቃት ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀሙ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና አካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረትም እንዲወድም ሆኗል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው” ብለዋል። እንዲሁም ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ሲቪል ሰዎችን ከጦርነቱ ሰለባነት የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲያከብሩና የድርጊቶቹን ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።ኮሚሽኑ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተጨማሪ አካባቢዎች ቀጣይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ የጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊ የሥነልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ መቅረቡን ጨምሮ በዚሁ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

ሙሉ የአማርኛውን ሪፖርቱን እዚህ ያገኙታል

የእንግሊዘኛውን ሪፖርት ከእዚህ ያውርዱ