የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን እየተከታተለ ይገኛል። በዚህም ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በተለይም በጸለምት/ጠለምት፣ በመጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ የሰዎችን የሕይወት፣ የአካል ደኅንነት፣ ነጻነት እና ንብረት መብቶች ሥጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን መረዳት ችሏል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ወደ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ሥጋት በመፈጠሩ ሳቢያ ነዋሪዎች ‘በኮማንድ ፖስት’ ሲተዳደሩ ከቆዩት አላማጣ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆኑን እንዲሁም በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደቦች መጣላቸውን ኢሰመኮ ተገንዝቧል፡፡
ይህ ግጭት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ሰፍኖ የነበረውን አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ወደ ኋላ የሚመልስ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ለተጨማሪ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚያጋልጥ ነው።
በመሆኑም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ በሲቪል ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ከማድረስ እንዲታቀቡ እንዲሁም ለግጭት መነሻ የሆኑ ልዩነቶችን በሕግ መሠረት በምክክርና በመግባባት ለመፍታት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ኢሰመኮ ያሳስባል። ማናቸውም እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ያከበሩ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በዓለም አቀፍና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነት እና የተመጣጣኝነት መርሖችን ያከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ኢሰመኮ ከመደበኛው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተፈጠረው ግጭት በውይይት የሚፈታበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግ ይገልጻል።