የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ከሚያከናውነው መደበኛ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ በተጨማሪ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት ዐውድ የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራዎችን በማከናወን ምክረ ሐሳቦችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በዚህም በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች  ላይ ከ20 በላይ ሪፖርቶች እና ሌሎች ሰነዶች ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ነው:: የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በተገኘው መረጋጋት ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ሥራውን በክልሉ ማከናወን የሚቀጥል ይሆናል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች እንደተገለጸውም ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ጋር (UNOHCHR) በጋራ መሥራት የሚቀጥሉበት አሠራር ለመዘርጋት እቅድ ተይዟል::