የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አንድምታና ተጽእኖ በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል። በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ያለ መሆኑን፤ በተለይም ሸዋ ሮቢት፣ አርማኒያ፣ አንጾኪያ፣ ገምዛ እና ማጀቴ በመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥና በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መኖሩን፤ በዚህም ምክንያት በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት የደረሰ መሆኑን እንዲሁም ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የተዘጋ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን መርተዋል/አስተባብረዋል የተባሉ የተወሰኑ ወጣቶች እና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች እንደታሰሩ ኢሰመኮ ተረድቷል።

ኢሰመኮ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት በሲቪል ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ጉዳት አድርሷል። በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ተጨማሪ ግጭቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ አስከፊ/ከባድ ጥሰቶች የሚያስከትሉ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ችግሩን በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ፣ ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲቆጠቡ፣ ስለደረሰው ጉዳት ሁሉ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም በማናቸውም ሁኔታ የሚፈጸሙ እስራቶች ሕግን መሠረት ያደረጉ በተለይም “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መሆን” የሚሉትን የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ያከበሩ መሆናቸውን መንግሥት እንዲያረጋግጥ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል።