የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ በሶማሊ ክልል እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የተመረጡ አካባቢዎች የትምህርት መብት አተገባበርን በተለይም የትምህርት ተገኝነትን እና ተስማሚነትን/ተለማጭነትን ለመገምገም ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ታኅሣሥ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር አካሂዷል። በውይይት መድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የመስኖና የቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ክትትሉ የተከናወነባቸው ክልሎች የትምህርት እና የአደጋ ሥጋት አመራር ቢሮዎች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ኢሰመኮ ትምህርት የማግኘት መብት በተለያዩ ዓለም አቀፍና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ያለውን ጥበቃ መሠረት በማድረግ የፌዴራል ተቋማትን ጨምሮ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያከናወነው ክትትል ግኝቶች እንዲሁም ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ክትትሉ ትምህርትን ለአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ተገኝ እንዲሁም ተስማሚ እና ከኑሮ ዘይቤያቸው ጋር የተጣጣመ ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎች ቢኖሩም አተገባበሩ ሰፊ ክፍተት እንዳለበትና የሚመለከታቸው አካላት የተቀናጀ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ያመላከተ መሆኑ ተገልጿል።

ተሳታፊዎች በአርብቶ አደር ማኅበረሰብ አካባቢዎች ትምህርት የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች የተወያዩ ሲሆን፣ በተለይም ከአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች የኑሮ ዘይቤ ጋር የሚጣጣሙ የትምህርት ሥርዓቶችንና ስልቶችን መቅረጽና ማስፋፋት፣ ጎጂ ባህሎችን መቅረፍ፣ የመሠረተ-ልማት አቅርቦትን ማስፋፋት እንደሚገባ ተገልጿል። በተጨማሪም የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ልዩ ፍላጎቶችን መሠረት በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እና በሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ተሰጥቷል።

የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሃዊ አስፈው በአርብቶ አደር አከባቢዎች የትምህርትን ተገኝነት፣ ተደራሽነት፣ ተቀባይነት እና ከአርብቶ አደሩ የኑሮ ዘይቤ ጋር ያለውን ተስማሚነት ለማረጋገጥ የመሠረተ-ልማት ዝርጋታን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም መብቱን በዘላቂነት እውን ለማድረግ ሁሉም አካላት ቅንጅታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።