የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በአፋር ክልል፣ ሰመራ ከተማ የሚገኙትን አጋቲና እና ሰመራ ካምፖች በተመለከተ ያካሄደውን ክትትል እና ያወጣውን ሪፖርት በማስታወስ፣ ይህንኑ ተከትሎ በካምፖቹ የነበሩ ሰዎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ተግባር መጀመር እና የባንክ አገልግሎት ማግኘትን ጨምሮ ሌሎች እየተደረጉ ያሉ ሰብአዊ ድጋፎችን በበጎ ተመልክቷል። ኮሚሽኑ በአማራ ክልል፣ ወሎ የሚገኙትን የጃራ እና የጃሬ ካምፖች በተመለከተ ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፣ ከአስተዳደራዊ እና የፀጥታ አካላት እያሰባሰበ ያለውን መረጃ የሚያካትት ሪፖርት በቅርቡ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።