በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አዘጋጅነት ላለፉት አራት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምስለ-ችሎት (Human Rights Moot Court) ውድድር ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተካሄደው የፍጻሜ ዝግጅት ተጠናቀቀ። በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ዙርያ ያተኮረው የዘንድሮው ውድድር በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ሆሳዕና፣ ሚዛን፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ እና ጎንደር ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን በ10 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 63 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 130 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡
በክልላዊ የቃል ክርክር ውድድሮች 1ኛ እና 2ኛ የወጡ 24 ተወዳዳሪ ቡድኖች የጽሑፍ ክርክራቸውን ለኢሰመኮ በመላክ የተወዳደሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ 8 ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከግንቦት 15-20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሩብ ፍፃሜ እና ግማሽ ፍፃሜ ዙሮች ተወዳድረዋል።
በግማሽ ፍፃሜና በሩብ ፍፃሜ የተወዳደሩ ትምህርት ቤቶች እና ተወዳዳሪዎች፡
- ተማሪ ሳያት ደሳለኝ እና ተማሪ አስቻለው ማቴዎስ ከወላይታ ሊቃ ት/ቤት
- ተማሪ ብሌን ሙሉጌታ እና ተማሪ አማኑኤል ዋሴ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮሙኒቲ ት/ቤት
- ተማሪ ለሚ ጎበና እና ተማሪ ሮቤ አህመድ ከኦሮሚያ ልማት ማኅበር አዳሪ ት/ቤት
- ተማሪ እንድሪያስ አድማሱ እና ሄለን ጌትነት ከአዘዞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት
- ተማሪ ማክዳ ዘውዱ እና ተማሪ ሰመተር አረብ ከማሪፍ ኢንተርናሽናል ት/ቤት
- ተማሪ ሜሮን አበበ እና ተማሪ ሂሬ ቢቂላ ከአዲስ ሕይወት ት/ቤት
- ተማሪ ሃቢባ ታጁዲን እና ተማሪ ሂራኒ ተውና ከእቴጌ መነን ት/ቤት
- ተማሪ አቢጊያ ነጻነት እና ተማሪ አብዱልሃሚድ መሃመድ በስራተ ገብርኤል ት/ቤት
ከወላይታ ከተማ፣ ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ሳያት ደሳለኝ እና ተማሪ አስቻለው ማቴዎስ እንዲሁም፣ ከጎንደር ከተማ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮሙኒቲ ት/ቤት የመጡት ተማሪ ብሌን ሙሉጌታ እና ተማሪ አማኑኤል ዋሴ ግማሽ ፍፃሜ አሸናፊዎች በመሆን ለፍፃሜ ውድድር ቀርበው ዛሬ በተደረጉው ውድድር ተማሪ ብሌን ሙሉጌታ እና ተማሪ አማኑኤል ዋሴ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮሙኒቲ ት/ቤት የሁለተኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምስለ-ችሎት ውድድር አሸናፊ ሆነዋል፡፡
የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የሚዳኝ ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር አይነት ነው። ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተመስርተው አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ነው።
የዘንድሮው ውድድር ምናባዊ ጉዳይም ትኩረቱን በሀገራችን አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ላይ ያደረገ ሲሆን በውስጡ የተፈናቃዮች መብቶችን በተለይም የአካል ጉዳተኞች መብቶች፣ የትምህርት መብት፣ ሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት፣ በመፈናቀል ወቅት የጠፉባቸውን ሰነዶች የማግኘት መብት፣ በቂ በሆነ የኑሮ ደረጃ የመኖር መብትን በማንሳት ተወዳዳሪ ተማሪዎች በመብቶቹ ዙሪያ ጥናት እንዲያደርጉና በቂ እውቀት እንዲያገኙ አጋጣሚ የፈጠረ ዝግጅት ነው፡፡
በፍፃሜ ዝግጅቱ ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት ተወካዮች፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተወካዮች፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች ቤተሰቦች እና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ እና መሰል ዝግጅቶች ታዳጊዎችን ስለ ፍትሕ ሥርዓት ከማስተማሩም ባሻገር የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል እና ለራሱና ለሌሎች ሰዎች መብቶች መከበር የሚቆም ትውልድን ለማፍራት ጉልህ ሚና አለው” ብለዋል።