የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመረቀቅ ሂደት ላይ ያለውን የአካል ጉዳተኞች ጥቅል ሕግ ለማዳበር ያለመ የልምድ ልውውጥ መድረክ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. አዘጋጅቷል፡፡

በመድረኩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች እና የጤና፣ ማኅበራዊ፣ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት፣  የሕግ ባለሙያ እና አካል ጉዳተኞች ማኅበር ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በዝግጅቱ ወቅት የአሜሪካ እና የዩጋንዳ የአካል ጉዳተኞች ሕጎች ማርቀቅ እና ትግበራ ሂደቶች እንዲሁም አሁን ያሉበት ደረጃ ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም በረቂቅ ሕጉ ዙሪያ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ ላይ በተነሱት ሐሳቦች ላይ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ልምዳቸውን ያጋሩት የአሜሪካ እና የዩጋንዳ ተወካዮች እንዲሁም  የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት የተከበሩ አቶ አዝመራ አንደሞ በመረቀቅ ሂደት ላይ ያለውን ሕግ ያላግባብ ከማጓተት ይልቅ የሀገሪቷን ዐቅም ባገናዘበ መልኩ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ማስከበር በሚቻልበት ሁኔታ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ በአፋጣኝ ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ንግግር በማድረግ ላይ
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ንግግር በማድረግ ላይ

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጥቅል ሕግ በማርቀቅ ሂደት ላይ እንደሆነ ጠቅሰው ኢሰመኮ ይኸው ሕግ የአካል ጉዳተኞችን ሙሉ ፍላጎት እና ጥቅም ሊያስከብር የሚችል ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። አክለውም ከዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ስምምነት ጋር የተጣጣመ ረቂቅ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች አዋጅ እንዲዘጋጅ፣ እንዲጸድቅ እና ወደ ሥራ እንዲገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡