የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን አስመልክቶ በ2017 ዓ.ም. የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ባካሄደው ክትትል ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሣሥ 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል። በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤን ጨምሮ የሕግ፣ ፍትሕ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የክልሉ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰላምና ጽጥታ ቢሮ፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ተወካዮች እንዲሁም ክትትሉ የተደረገባቸው 5 ማረሚያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።


በውይይቱ በምክረ ሐሳቦች ትግበራ ክትትል የተለዩ መልካም ሁኔታዎች እና መሻሻል የሚገባቸው ግኝቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በማረሚያ ቤቶች የመጠጥ እና ንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት ችግር መፈታቱ፣ ለታራሚዎች ግልጽ የቅሬታ ማቅረቢያ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ፣ ሴት ታራሚዎች በገቢ ማስገኛ፣ በትምህርት እና ልዩ ልዩ ሙያዎች ሥልጠና ላይ ያላቸው ተሳትፎ መሻሻሉ፣ ለሴት ታራሚዎች የግል ንጽሕና መጠበቂያ ከግል ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑ፣ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤት በሚገቡበት ጊዜ የጤና ምርመራ የሚደረግላቸው መሆኑ እና የማደሪያ ክፍሎች ንጽሕና በየጊዜው ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑ እንዲሁም በደብረ ብርሃን ማረሚያ ቤት ሞዴል የወጣት ታራሚዎች ማረሚያ ቤት ለመገንባት 17,000 ካሬ ሜትር ቦታ ርክክብ ተደርጎ የግንባታ ማስጀመሪያ መሠረት መጣሉ ክትትሉ በመልካም አፈጻጸም ከለያቸው መካከል ተጠቅሰዋል።


በሌላ በኩል የኮምቦልቻ ማረሚያ ቤት ቅጥር ግቢ መጥበብ ለታራሚዎች መጨናነቅ ምክንያት መሆኑ፣ ከፍተኛ ሕመም ያጋጠማቸው ታራሚዎች ወደ አዲስ አበባ ሄደው ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸው፣ ለአንድ ታራሚ የተመደበው የቀን የምግብ በጀት ብር 55 አሁን ላይ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር በቂ አለመሆኑ እና በሐኪም የሚታዘዝ ልዩ ምግብ ከበጀት ጋር በማያያዝ አለመፈጸም፣ ታራሚዎች ከማረሚያ ቤት ውጭ ላላቸው ጉዳይ የጉዳይ አስፈጻሚ ባለሙያ አገልግሎት አለማግኘታቸው፣ እንዲሁም እንደ ስፖርት ማዘውተሪያና ካፍቴሪያ ያሉ የጋራ መገልገያዎች የውስጥ ገቢን ለማሳደግ በከፍተኛ ዋጋ ለነጋዴዎች በጨረታ መሰጠታቸው ታራሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸው ትኩረት የሚሹ እና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ክትትሉ አመላክቷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ ኢሰመኮ በክትትሉ በዝርዝር የለያቸውን ግኝቶች እና የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች በበጎ እንደሚቀበሉትና የክልሉ ምክር ቤት በሚያከናውናቸው የክትትል ሥራዎች ሪፖርቱ በግብዓትነት እንደሚያገለግል ግልጸዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ ከኢሰመኮ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ጠቅሰው ክልሉ በግጭት ውስጥም ቢሆን ሰብአዊ መብቶች በማንኛውም ጊዜ ተከብረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጠዋል።

የኢሰመኮ ባሕር ዳር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር አማረ ተስፋዬ ኢሰመኮ በምክረ ሐሳቦች ትግበራ ክትትል ወቅት የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ማስፋፋት እና ችግሮችን ማረም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለደርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት በክልሉ ያለውን የታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ማሻሻል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ሪጂናል ዳይሬክተር ዮናስ ሙሉጌታ በበኩላቸው ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ ታርመውና ታንጸው እንዲወጡ ማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረት የሚፈልግ በመሆኑ ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።