የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ መልክ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚፈጸመውን የበርካታ ሰዎች እስር በተመለከተ ክትትል ማድረጉን የሚቀጥል ሲሆን፣ በማናቸውም ወቅት ቢሆን የሚፈጸም እስር ተገቢውን የሕግ እና የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ሊከተል የሚገባ መሆኑን ያሳስባል። የመንግሥት ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና የሚዲያ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ወደ ጊዜያዊ ማቆያዎች እየተወሰዱ ሲሆን፣ እስሮቹ በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ያልተፈጸሙ፣ ተጠርጣሪዎቹ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆናቸው እንዲሁም ከመካከላቸው ቋሚ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ ተችሏል። የጊዜያዊ ማቆያዎቹን ሁኔታ እንዲሁም የተያዙ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ የሚመለከታቸውን የክልሉን የአስተዳደር እና ጸጥታ አካላት ለማነጋገር እና ምላሽ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል ይሆናል።
እንዲሁም ኢሰመኮ መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን አድቬንቲስት ትምህርት ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ላይ ለጊዜው ማንነታችው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙት የቦንብ ፍንዳታዎች ያደረሱትን የሰብአዊ ጉዳት እና አንድምታ እየተከታተለ ሲሆን፤ ማንኛውም አካል በሲቪል ሰዎች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከማድረስ እንዲሁም የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሚያውክ ተግባር ሊቆጠብ እንደሚገባ ያሳስባል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የሚፈጸሙት እስሮች በታሳሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖ እንዲሁም በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን የእምነት መሸርሸር አስታውሰው፣ “በትጥቅ ግጭት እና በጸጥታ መደፍረስ ወቅትም ቢሆን ሲቪል ሰዎችን ለመያዝ የሚያበቃ/በወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ሕጋዊ ምክንያት መኖሩን፣ የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው በፍርድ ቤት የተሰጠ የመያዣና የብርበራ ትእዛዝ መኖሩን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ብቻ እና መብቶቻቸውን ባከበረ ሁኔታ መያዛቸውን እንዲሁም በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።