ሁሉንም ሰዎች አስገድዶ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን እንደሚያስቀምጠው፤ ማንኛውም ሰው አስገድዶ ከመሰወር ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል።
ማንኛውም አይነት ልዩ ሁኔታ፤ ማለትም ጦርነትም ሆነ የጦርነት ስጋት፣ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም ማንኛውም ሌላ ሀገራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወይም አደጋ መከሰት የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ለመፈጸም በምክንያትነት ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ (አንቀጽ 1)
በኮንቬንሽኑ መሰረት፤
በመንግሥት ወኪሎች ወይም በመንግሥት ፈቃድ፣ ድጋፍ እና እውቅና ስር በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚፈጸም እስር፣ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ ጠለፋ ወይም ማንኛውም አይነት ነፃነትን የማሳጣት ድርጊት፤ በተጨማሪም የሰዎችን ነፃነትን የማሳጣት ድርጊት ወይም እስር ስለመፈጸሙ ባለማመን ወይም ለማሳወቅ ፈቃደኛ ባለመሆን፤ ወይም የጠፋውን/የተሰወረውን ሰው እጣፋንታ ወይም ያለበትን ቦታ በመደበቅ ሰዎችን ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ አስገድዶ መሰወር እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ (አንቀጽ 2)
ኢትዮጵያ ሁሉንም ሰዎች አስገድዶ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣውን ኮንቬንሽን ገና ያላጸደቀች ቢሆንም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ (ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን በአባል ሀገራቱ ያለውን አተገባበር የሚከታተል የገለልተኛ ባለሙያዎች ኮሚቴ)፤ ይህንኑ ትርጓሜ በማስታወስ፣ የአንድ ሰው መሰወር የበርካታ ሰብአዊ መብቶችን ጥሰት መሆኑንና የቤተሰቦችን መብቶችን ጭምር እንደሚጥስ በተጨማሪነት ያስረዳል፡፡