የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት ወደ መደበኛ የትምህርት ሥርዓት እንዲመለሱ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለተፈናቃይ ሕፃናት አካታች፤ ተደራሽ እና ተቀባይነት ያለው የመማር ዕድል ማረጋገጥን አስመልክቶ፤ ከፌዴራል እና ከክልል የመንግሥት ተቋማት፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኢምባሲ እና የዓለም አቀፍ ልማት ተቋማት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ባለሙያዎች ጋር መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አድርጓል።

የውይይት መድረኩ “ትምህርት ጊዜ አይሰጥምና ከትምህርት ገበታ ውጪ ለሆኑት የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት አካታች፣ ተደራሽ እና ተቀባይነት ያለው የመማር ዕድል ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነው፡፡  በውይይት መድረኩ፤ በመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናት የመማር ዕድል ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶች እና ምቹ አጋጣሚዎች ምን እንደሚመስሉ፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት የትምህርት ተደራሽነት እና አካታችነት በማረጋገጥ ረገድ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ስላላቸው ሚና፤ ለተፈናቃይ ሕፃናት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ሉሚነስ ፈንድ፣ ዩኒሴፍ እንዲሁም አፍሪካን ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት እንዲሁም መልካም ተሞክሮዎች ዙሪያ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት የትምህርት ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ኢሰመኮ ባከናወናቸው የክትትል ሥራዎች በተለዩ አንኳር የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ እና ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ዙሪያ ወደ ፊት ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ምክክር የተደረገ ሲሆን፤ ተፈናቃዮችን ወክለው የቀረቡ ተሳታፊዎችም በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተፈናቃይ ሕፃናት የትምህርት ተደራሽነት ነባራዊ ሁኔታ እና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ እይታቸውን ለተሳታፊዎች አጋርተዋል። በዚህም በመፈናቀል ወቅት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ በዋነኝነት የነፍስ አድን ድጋፍ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የትምህርት ጉዳይ የተዘነጋ እንደሆነ፣ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት እንደ አንድ መሠረታዊ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት አለመታየቱ፣ ትምህርት ቤቶች እንደ ጊዜያዊ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እያገለገሉ መሆኑ፤ የሰሜኑ ጦርነትን ጨምሮ የተለያዩ ግጭቶችን ባስተናገዱ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመውደማቸው እና ጉዳት የደረሰባቸው በመሆኑ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረገው ጥበቃ እና ድጋፍ የተሟላ አለመሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ “ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በግጭትና በጦርነት ሳቢያ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመት ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 1093 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ፤ 3220 በከፊል ወድመዋል፤ 4.7 ሚሊዮን ተማሪዎች እና 185ሺ መምህራን ደግሞ ከመማር-ማስተማር ገበታ ተፈናቅለዋል” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። “ይሁንና መንግሥት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር 7749 ጊዜያዊ የመማሪያ ቦታ ማዘጋጀትና ለ35013 መምህራን የሥነ-ልቦና ስልጠና መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ 78 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ መደረጉን” አክለው ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የውይይት መድረኩ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት የትምህርት ተደራሽነትን፤ አካታችነትን እና ተቀባይነትን ለማረጋገጥ ያሉ ዕድሎችን፣ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያሳየ ነበር፡፡

ለአንድ ቀን የተደረገው የውይይት መድረክ በመፈናቀል ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ሕፃናት በአስቸኳይ የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ፤ ወደ መደበኛ የትምህርት ሥርዓት እንዲመለሱ እንዲሁም አካታች፤ ተደራሽ እና ተቀባይነት ያለው የመማር ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት፤ በቀጣይ በፌዴራል መንግሥት ተቋማት እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሚያስተናግዱ ክልሎች እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ የዓለም አቀፍ እርዳታ እና ልማት ድርጀቶች ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በመለየት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡