የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች ሥር በሚገኙ 46 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 5 ማረሚያ ቤቶች ላይ ባካሄዳቸው ክትትሎች፣ በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 19 እና 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሳይታ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የአፋር ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የክልሉ ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አባላት፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ እና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ በክትትሉ የተለዩ መልካም ተሞክሮዎች እና መሻሻል የሚገባቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉ፣ ተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ከጠያቂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሳምንቱን በሙሉ የሚገናኙበት አሠራር መዘርጋቱ፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች ለተጠርጣሪዎች ምግብ እና ሕክምና የሚሆን በጀት መመደብ መጀመሩ እንዲሁም ለታራሚዎች ምግብ እና ሕክምና አገልግሎት የተመደበው በጀት ከፍ እንዲል መደረጉ በውይይቱ በአዎንታዊነት ተነስተዋል።

በሌላ በኩል በፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ማቅረብ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወጣት ተጠርጣሪዎች ከአዋቂዎች ተለይተው የሚያርፉባቸው ክፍሎች አለመኖራቸው እንዲሁም የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያንን ፍላጎቶች ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ልዩ ድጋፎች አለመኖር፣ የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች እጥረት በመኖሩ የተጣበቡ መሆናቸው እና የአምቡላንስ አገልግሎት አለመኖር ሊሻሻሉ የሚገባቸው አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የቀረቡት ግኝቶች በፖሊስ ጣቢያ እና ማረሚያ ቤቶች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ መሆናቸውን አንስተው በክትትሎቹ የተለዩ አዎንታዊ ሁኔታዎችን ለማስቀጠል እንዲሁም በአሳሳቢነት ለተጠቀሱ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ የተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካልት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። አክለውም ኢሰመኮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።