የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል በዞን ሁለት (ኪልበቲ ረሱ)፣ በረሐሌ፣ አብአላ እና መጋሌ ወረዳዎች በሚገኙ በ6 መጠለያ ጣቢያዎች፤ በሰመራ ከተማ በሰመራ ስታዲየም ውስጥ የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዲሁም በዞን አራት (ፈንቲ ረሱ) በጉሊና፣ ያሎ ወረዳዎች እና በዞን ሁለት አብአላ ወረዳ ጉቤ ቀበሌ የሚገኙ ተመላሾች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ከኅዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ክትትል አከናውኗል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በመፈናቀል ሂደት የቤተሰብ አባሎች ሞት፣ አካል ጉዳት እና ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸው መሆኑን፤ ቤቶቻቸው፣ ንብረቶቻቸው እና ከብቶቻቸው መውደማቸውንና መዘረፋቸውን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድን በሚመለከት፤ ሰዎች ከመፈናቀላቸው በፊት በቀበሌው የሚገኘውን የነዋሪ ብዛት መጠን በቤተሰብ ደረጃ መረጃ ከመያዝ ባሻገር በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚኖሩ ተፈናቃዮች እና ተመላሾች ምዝገባ እንዳልተከናወነ እና የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ጨምሮ ሌሎች ሰነዶችን የመስጠት አገልግሎት አለመጀመሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ ለማወቅ ችሏል፡፡
በተጨማሪም በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዳግም ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፤ የጦርነት ቀጠና የነበሩ እንደ ጉሊና ወረዳ ፎኪሳ ቀበሌ ባሉ አካባቢዎች ፈንጂ እና መሰል የጦር መሣሪያዎችን በማምከን አካባቢውን ከአደገኛ የጦር መሳሪያዎች የማጽዳት ሥራ በአግባቡ ባለመከናወኑ በተመላሾች ላይ የደኅንነት ሥጋት ፈጥሮባቸዋል፡፡
ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች ተመላሾች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ የተመለሱ ቢሆንም፤ መደበኛ ኑሯቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በተመለከተ ክፍተቶች እንዳሉ የኮሚሽኑ ክትትል ያመላክታል፡፡ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት እና ዞን አራት በኩል በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዘው ይገቡ የነበሩ ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እንዳይገቡ የተጣለው እገዳ ባለመነሳቱ በሁለቱ ዞኖች ውስጥ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ከመገደቡ በተጨማሪ በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል። ይህም በአካባቢው ለተደጋጋሚ መፈናቀል የተዳረጉ ነዋሪዎች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የቆየው ግጭት ካስከተለባቸው የሰብአዊ ቀውስ በተጨማሪ በቂ እና ወቅቱን የጠበቀ የሰብአዊ ድጋፍ ካለመቅረቡ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴው ገደብ ባለመነሳቱ ምክንያት እየደረሰባቸው ያለው ያልተገባ ኢኮኖሚያዊ ጫና፤ ተፈናቃዮች እና ተመላሾች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳይፈጠር ተግዳሮት ሆኗል።
ኢሰመኮ ባከናወነው ክትትል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ተመላሾች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ የሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ተመልክቷል፡፡ በተለይ በጦርነቱ ወቅት የሕክምና ቁሳቁሶች፣ የመድኃኒቶች እና የክትባት ማስቀመጫ ፍሪጅን ጨምሮ በርካታ የጤና አገልግሎት ተቋማት በመዘረፋቸውና በመውደማቸው የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት እጥረት ፈጥሯል። በተመሳሳይ ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ ለሚሹ ተፈናቃዮች ማለትም ለሚያጠቡ እናቶች፣ ነፍሰጡሮች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ተጓዳኝ ሕመም ላለባቸው ተፈናቃዮች የመብቶች ጥሰት ተጋላጭነታቸውን እና ልዩ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ የሰብአዊ ድጋፍ እንደማይቀርብ፣ ለሕፃናት እና አጥቢ እናቶች የሚሰጥ የተለየ የምግብ ድጋፍ ስለሌለ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ መኖራቸውን ኮሚሸኑ ባደረገው ክትትል ተገንዝቧል፡፡
ኮሚሽኑ ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች የነበረውን አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከለየ በኋላ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት የሁኔታውን አሳሳቢነት የሚገልጽ በተለይ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን እና የዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በተመለከተ የተስተዋሉ ክፍተቶች እንዲታረሙ በቃል እና በጽሑፍ ምክረ ሐሳቦችን በማጋራት ሁኔታው እንዲሻሻል ሲወተውት ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዲሁም በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አደጋ ሥጋት አመራርና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስተባባሪነት ክትትሉ በተደረገባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ተፈናቃዮች ምግብ እና ምግብ-ነክ ያልሆኑ የሰብአዊ ድጋፎች እንደቀረቡ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ኢሰመኮ በድጋሚ ባደረገው ማጣራት ለተፈናቃዮች የተሰራጩ የሰብአዊ ድጋፎች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ ባለመሆናቸው በተፈናቃዮች ሁኔታ ላይ ተጨባጭ መሻሻል አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “በክልሉ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰሜኑ ጦርነት ካስከተለባቸው የሰብአዊ ቀውስ በአግባቡ ለማገገም እና እራሳቸውን ችለው ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት የንግድ እንቅስቃሴ ገደቡ አለመነሳቱ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረባቸው እና መደበኛ ኑሯቸውን እንዳይቀጥሉ ከማድረጉ ባሻገር በዘላቂነት እንዳይቋቋሙ እንቅፋት ሆኗል” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። አክለውም “የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታት እንደአስፈላጊነቱ ለጋሽ ድርጅቶችን በማስተባበር እየተሰጠ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ በማጠናከር ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮችን ታሳቢ ያደረገ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ፤ እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።