“ወደ ኬንያ ዋጂር የመጣሁት የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ነበር፡፡ ግን ያሰብኩት ሳይሳካ ለእስር ተዳረኩ፡፡ የትውልድ ስፍራዬ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ ወላይታ ዞን፣ ዱጉና ፋንጎ ነው፡፡ ሞያሌ ሄጄ እየሰራሁ ሳለ ነው አንድ ደላላ ያገኘኝ፡፡ ዋጂር የሚባል በኬንያ የሚገኝ ከተማ ያለ የእርሻ ቦታ ሄጄ ብሰራ የተሻለ ገንዘብ እንደማገኝ ነገረኝ፡፡ በሞያሌ አካባቢ የነበረው የጎሳ ግጭት እና የሰማሁት የተሻለ የስራ እድል በአንድ ላይ ተዳምሮ ወደ ዋጂር እንድሰደድ ምክንያት ሆኑኝ፡፡ ወደ ዋጂር ከመጣሁ ሁለት ዓመት ቢሆነኝም በቂ ገንዘብ ግን ገና አልሰራሁም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተይዤ ወደ ሞያሌ እንድመለስ ሲደረግ ይህ አምስተኛዬ ነው፡፡ ወደ ዋጂር ላሻገረህ ደላላ ክፍያ ከፍያለሁ ብሎ አሰሪዬ ስሰራለት የቆየሁበትን የተወሰነውን ክፍያ ከልክሎኛል፡፡ እዚህ ስመጣ የኔን እና የቤተሰቦቼን ሕይወት እለውጣለሁ የሚል ትልቅ ህልም ይዤ ነበር የመጣሁት፡፡ አሁን ግን ህልሜ እንደተሰበረ ይሰማኛል፡፡ ሆኖም ወደ ቤተሰቦቼ ባዶ እጄን መመለስ አልፈልግም፣ አላደርገውም፡፡” ይህ የአስፋው ታሪክ ነው፣ አስፋው በዋጅር ፖሊስ ጣቢያ ተይዞ የነበረ እና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የተወሰነበት የ17 ዓመት ኢትዮጵያዊ ፍልሰተኛ ነው፡፡

ከኢሰመኮ ወደ ኬንያ ለሥራ የተጓዘው ቡድን በዋጂር ከተማ፣ ኬንያ የሚገኘውን የፖሊስ ማቆያ ጣቢያ የጎበኘ ሲሆን በማቆያ ጣብያው በእስር ላይ የሚገኙ 9 መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞችን አነጋግሯል፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ናቸው የተባሉ ሲሆን አራቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሕጻናት መደበኛ ላልሆነ የፍልሰት አዙሪት የተጋለጡ ሲሆን ይህም የሰብአዊ መብቶቻቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ፣ በሕገወጥ ደላሎች እና በሙስና ለተዘፈቁ ባለሥልጣናት ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ ሌሎች ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 18 መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞችም በዋጂር እስር ቤት በእስር ላይ እንደሚገኙ ቡድኑ ለማወቅ ችሏል፡፡ 

ኢሰመኮ በጎረቤት ሀገራት ከሚገኙ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ የፍልሰተኞች አስተዳደር ማስተዋወቅን ዓላማው አድርጎ ዘላቂ የልማት ግብ 10.7ን ለማሳካት ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ስርአት ያለው እና መደበኛ የሆነ ፍልሰትን ለማሳካት እየሰራ ይገኛል፡፡