ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በኅዳር እና በታኅሣሥ ወራት 2014 ዓ.ም.  የሚውሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች አስበው እንደሚውሉ ገለጹ። ኢሰመኮ በተለይም ከእ.ኤ.አ. ከኅዳር 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሚታሰቡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀናት #ጤናማቃላት ወይም #KeepWordSafe የሚል የማኅበራዊ ድረ ገጽ እንቅስቃሴ “ሃሽታግ” እና ታስበው የሚውሉትን ዓለም አቀፍ ቀናት ማሳወቁ ይታወሳል።   

በዚህም መሰረት “ለእኩልነት፣ መድሎን ለመቀነስ እና ሰብአዊ መብቶችን ለማሳደግ “ በሚል መሪ ቃል ለ73ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም የሰብአዊ መብቶች ቀን ከኅዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 6  2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በጋራ የሚያከብሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር- የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ጽ/ቤት (OHCHR- EARO)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) እና አምስት አባላቶቹ (የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA)፣ ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዲሞከራሲ (ቪኢኮድ / (VICOD)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ ሴንተር ፎር ጀስቲስ (Centre for Justice)፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ማኅበር ከኅዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 6 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በዋና ዋና የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄዎችና ዝግጅቶች ያዘጋጃሉ። 

በዚሁ አጋጣሚ በኢሰመኮ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ፣ በአዳማ እና በሀዋሳ ከተሞች እንደሚዘጋጅ ተገልጿል። 

በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ለእይታ እና ለውይይት የሚቀርቡበት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ግንዛቤ ለማዳበር ሰፊ ተደራሽነት ያለውን የፊልም ጥበብ እንደአንድ መንገድ መጠቀም ዓላማው አድርጓል፡፡ በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ከዚህ በፊት ለእይታ የበቁ እና አዳዲስ የሙሉ ጊዜ፣ አጫጭር እና ዘጋቢ ፊልሞች ለእይታ ይቀርባሉ፡፡  

በሴቶች እና የሕጻናት መብቶች፣ በአካል ጉዳተኝነት እና በአረጋውያን መብቶች ጥበቃ እና እንክብካቤ፣ የመደራጀት እና የመንቀሳቀስ መብቶች፣ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እና መረጃ የማግኘት መብት፣ በሕይወት የመኖር መብት፣ በሕግ እኩል ጥበቃ የማግኘት እና ፍትሕ የማግኘት መብቶች፣ በባሕል መብት ስርም በራስ ባሕል የመሳተፍ፣ በእኩልነት ሰብአዊ ክብርን በጠበቀና ከመድሎ በጸዳ መልኩ በራስ ቋንቋ የመማር መብቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ይቀርባሉ፣ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኅዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ ኦሊያድ ሲኒማ፣ በኅዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ሌዊ ሲኒማ በመጨረሻም በታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በጋርደን ግሩቭ ዎክ መናፈሻ የሚካሄድ ሲሆን፣ በፌስቲቫሉ ላይ ጥሪ የሚደረግላቸው የፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የሚገኙ ባለሞያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሰሩ ተቋማት፣ ሚዲያዎች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ፍላጎቱ ያላቸው ተመልካቾች ይታደሙበታል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚካሄዱ ዝግጅቶች መካከል የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ጥያቄና መልስ ውድድርና ፌስቲቫሎች፣ የማረሚያ ቤቶችን ጉብኝትና ነጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከል ምርቃት፣ የሰላም ግንባታና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የተመለከቱ የፓናል ውይይቶችን እና ኮንፈረንሶችን እንዲሁም የእውቅና ሽልማቶችን መስጠት ይገኙበታል፡፡ 

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ሁሉም ተባባሪ ድርጅቶች በጋራ የሚያዘጋጁት መርኃ-ግብር ጊዮን ሆቴል በሚገኘው ጋርደን ግሩቭ ዎክ መናፈሻ ይካሄዳል። በዚህ የጋራ ዝግጅት ላይ የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ-ቃል ዋና መልዕክት የሚተዋወቅ ሲሆን፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን የሚያስተዋውቅ ባሕልና እሴት ላላቸው ማኅበረሰቦች ዕውቅና የሚሰጥ ይሆናል።

ዝርዝር መርኃ ግብሩ እዚህ ተያይዟል::