የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (Human Rights Moot Court) ፍጻሜ ውድድር ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ፡፡ ውድድሩ ከመጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልል እና ሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ በ10 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 72 ትምህርት ቤቶች እና 144 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።

በውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ 8 ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከግንቦት 13 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው ሀገር አቀፍ የቃል ክርክር ውድድር በሩብ እና በግማሽ ፍጻሜ ዙሮች ሲሳተፉ ቆይተው በዛሬው ዕለት የፍጻሜ ውድድር አድርገዋል፡፡

በግማሽና በሩብ ፍጻሜ የተወዳደሩ ትምህርት ቤቶች እና ተወዳዳሪዎች፡-

  1. ከአሶሳ ኦሞሻ ከተማ ፋሮ ፋውንዴሽን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት (ተማሪ ኑሃሚን አስቻለው እና ተማሪ ስምረት ያይኑ)
  2. ከሚዛን ቴፒ ከተማ ሚዛን ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ማቲዎሰ መሀሪ እና ተማሪ ናርዶስ ብርሃኑ)
  3. ከድሬዳዋ ሳቢያን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ፍሮምሳ ኡስማን እና ተማሪ ነስቲሆ ፋራህ)
  4. ከደብረ ማርቆስ ከተማ ሐዲሰ አለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት (ተማሪ ጌታሁን ስሜነህ እና ተማሪ ፌቨን ሀብቴ)
  5. ከሃዋሳ ኤስ ኦ ኤስ (SOS) ትምህርት ቤት (ተማሪ በረከት ታምራት እና ተማሪ ናዝራዊት ከበደ)
  6. ከኦዳ አዳማ አዳሪ ትምህርት ቤት (ተማሪ ሜቲ ገመቹ እና ተማሪ ዮናስ ብርሃኑ)
  7. እና ፈትሒያ ኢስሃቅ)
  8. ከወልቂጤ ያበሩስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ጽዮን እርቁ እና ተማሪ ዳዊት ሰሎሞን) ናቸው፡፡

ለፍጻሜ ውድድሩ የደረሱት ተወዳዳሪ ተማሪዎች ከያበሩስ ወልቂጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ጽዮን እርቁ እና ተማሪ ዳዊት ሰሎሞን፤ እንዲሁም ከሃዋሳ ኤስ ኦ ኤስ (SOS) ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ በረከት ታምራት እና ተማሪ ናዝራዊት ከበደ ናቸው።

በዚሁ መሠረት በተደረገው የፍጻሜ ውድድር ተማሪ በረከት ታምራት እና ተማሪ ናዝራዊት ከበደ ከሃዋሳ ኤስ ኦ ኤስ (SOS) ትምህርት ቤት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም የውድድሩ ምርጥ የቃል ተከራካሪ በመሆን ተማሪ ፈትሒያ ኢስሃቅ ከሐረሪ ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ያሸነፈች ሲሆን በምርጥ የጽሑፍ ክርክር ደግሞ ከያበሩስ ወልቂጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ጽዮን እርቁ እና ተማሪ ዳዊት ሰሎሞን አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

የዘንድሮው ውድድር ምናባዊ ጉዳይ ትኩረቱን በወንጀል ድርጊት ተሳትፎ የተጠረጠሩ ሕፃናት ላይ አድርጓል፡፡ ምናባዊ ጉዳዩ በውስጡ በወንጀል የተጠረጠሩ ሕፃናት የቅድመ ክስ እስራት፣ የጅምላ እስር፣ በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ወሰን ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት፣ ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር ያለመታሰር መብት፣ በቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው እና ጠበቆቻቸው የመጎብኘት መብት፣ በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት መብት፣ ኢሰብአዊ ከሆነ እና የሰብአዊ መብቶች መለኪያን ከማያሟላ አያያዝ የመጠበቅ መብትን በማንሳት ተወዳዳሪ ተማሪዎች በመብቶቹ ዙሪያ ጥናት እንዲያደርጉ እና ዕውቀት እንዲያካብቱ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡

የምስለ ችሎት ውድድር በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የሚዳኝ እና ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር ዓይነት ነው። ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተመሥርተው አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ነው።

በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተወካዮች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በውድድሩ መክፈቻ ላይ ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በሰብአዊ መብቶች መርሖች እና እሴቶች የታነጸ ትውልድ ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ተማሪዎቹ ወደፊት ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸው የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ መሰናክሎች ቢያጋጥሟቸው እንኳን በጽናት፣ ሁሌም የተሻለ ነገን በማለም እና በጋራ በመሥራት ህልማቸውን ማሳካት እንደሚችሉ የሕይወት ተሞክሯቸውን በማካፈል ተማሪዎቹን አበረታተዋል።