የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (United Nations Human Rights Council – UNHRC) ላይ በምታቀርበው ሁሉ-አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ወቅታዊ ግምገማ (Universal Periodic Review- UPR) ረቂቅ ሪፖርት ላይ ከባለድርሻዎች ጋር ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል። ረቂቅ ሪፖርቱ በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በተገኙበት ለውይይት ቀርቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ የግምገማ መድረክ (UPR) በተ.መ.ድ. የጠቅላላ ጉባኤ በመጋቢት ወር 1998 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን ተቀብለው እና አጽድቀው የሀገራቸው የሕግ አካል ያደረጉ አባል ሀገራት የገቡትን ቃል አተገባበር እና አፈጻጸም ደረጃ እርስ በራሳቸው የሚገማገሙበትና እና ተቀብለው ያላጸደቋቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲፈርሙ ምክረ ሐሳብ የሚለዋወበት መድረክ ነው። ሂደቱን በየ2 ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ የሚመረጡ 47 ሀገራት አባል የሆኑበት የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (UNHRC) ያስተባብረዋል።
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ 4ኛ ዙር ሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ የግምገማ መድረክ ላይ የምታቀርበው ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2019 3ኛ ዙር ሪፖርት ባቀረበችበት ወቅት የተሰጧትን ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ክትትል፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በማሻሻል ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሠሩ ሥራዎችን በዝርዝር የሚያስረዳ መሆን ይጠበቅበታል። በዚሁ መሠረት የውይይት መድረኩ በረቂቅ ሪፖርቱ የሚካተቱ የቅርብ ጊዜ መረጃን ለመሰብሰብ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት መሠረት ግዴታዋን በትክክል እየተወጣች ስለመሆኑ ለመለየት፣ ያልተካተቱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እንዲካተቱ እና የሚቀርበው ሪፖርት የበለጠ ሀገራዊ ሁኔታውን የሚገልጽ ለማድረግ ግብአት ለመሰብሰብ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይት መድረኩ የሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ ረቂቅ ሪፖርት ማብራሪያ ቀርቦ፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው እና ያላጸደቀቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ለሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ የግምገማ መድረክ ያቀረበቻቸው ሪፖርቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ተዳስሰዋል። በ3ኛ ዙር በቀረበው ሪፖርት ላይ 327 ምክረ ሐሳቦች ለኢትዮጵያ የተሰጡ መሆናቸውን፤ ከእነዚህም መካከል 270 ምክረ ሐሳቦችን እንደተቀበለች እና 57ቱን ደግሞ ከግምት ውስጥ እንደምታስገባ ማሳዋቋ ተገልጿል። ማብራሪያውን ተከትሎ ተሳታፊዎች ከሚመለከታቸው የሰብአዊ መብቶች ዘርፍ አንጻር በ4 ቡድኖች ተከፍለው በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ውይይት በማድረግ አስተያየት እና ግብአት ሰጥተዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ሀገሪቱ የተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለማ አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ተቀብላ ማጽደቋን ጠቅሰው፣ እነዚህን ስምምነቶች መቀበል ደግሞ መብቶችን ማክበር፣ ማስከበር እና ማስፋፋት እንዲሁም ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ ኢትዮጵያ ለ4ኛ ጊዜ የምታቀርበው ሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ ሪፖርት ይሄን ግዴታ የመወጣት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው ሁሉ-አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና አጠባበቅ ክፍተት ለመለየት እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ልምድ ለመቅሰም ያለውን ጠቀሜታ ጠቁመው፣ ለ4ኛ ዙር በሚቀርበው ሪፖርት መካተት የሚገባቸው ነጥቦች በአግባቡ እንዲነሱ ኢሰመኮ እንደ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም እንዲህ ያሉ አስቻይ መድረኮችን መፍጠር እና እገዛ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ሁሉ-አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ወቅታዊ ግምገማ ሪፖርት ዝግጅት ሂደት ግልጽ እና አሳታፊ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል።