የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎችን ከሕግ ውጪ መያዛቸውን በተመለከተ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በዚህም፣ ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ፣ “ለምልመላ” በሚል ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ የተሳተፉ፣ የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁ ወይም የተቀበሉ እንዲሁም ይህንን ድርጊት የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የጸጥታና አስተዳደር አካላት ላይ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስቧል። በተጨማሪም ኢሰመኮ በቀጣይ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚከናወኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሰራዊቱ መስፈርቶችና የአሠራር ሥርዓቶች መሠረት ብቻ ሕግን በተከተለ እና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሁኔታ መከናወናቸው እንዲረጋገጥ ምክረ ሐሳብ የሰጠ መሆኑ ይታወሳል።

ኢሰመኮ በምርመራው ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ እና ከውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና አባላት ጋር ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምክክር አካሂዷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሚኒስቴርም በሁሉም ክልሎች የሚከናወኑ የሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሕግ በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት ብቻ የተከናወኑ ስለመሆናቸው በማረጋገጥ የሚረከብ መሆኑን ለኢሰመኮ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በደረሰው ደብዳቤ ገልጿል። በተለይም በ2017 ዓ.ም. እየተደረገ ያለውን ምልመላ አፈጻጸም ለመፈተሽ ከከፍተኛ ሙያተኛ መኮንኖች የተውጣጣ ከ7 እስከ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ በማጣራት መስፈርቶቹን የሚያሟሉትን ብቻ ለይቶ ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት ማስገባቱን እና ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በክልሎች በተከናወነው የምልመላ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ካሉ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ለማጣራት የሚቻል መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል። ስለሆነም ኢሰመኮ ክልሉ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ እና በቀጣይ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያደርገውን ጥረት እና ውትወታ ይቀጥላል።

በሌላ በኩል ኢሰመኮ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የተሰራጩ የተወሰኑ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ተመልክቷል። በሪፖርቱ እንደተመላከተው ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ጉዳይ በዋናነት በግዳጅ ምልመላ (conscription) ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 መሠረት በነጻነት መብት ማዕቀፍ እንዲሁም የሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስራት ክልከላን በሚመለከቱ ድንጋጌዎች መሠረት የሚታይ መሆኑን በድጋሚ ይገልጻል።