የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ 

ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት አርዳ ጅላ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሕይወትና የአካል ጉዳት ስለመድረሱ በደረሰው ጥቆማ መሰረት፣ ከታኅሣሥ 7 እስከ ታኅሣሥ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በቦታው በመገኘትና ተጎጂዎችን፣ የአይን እማኞችን፣ የሟች ቤተሰቦችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በማነጋገር ምርመራ አካሂዷል። 

በዚህም መሰረት ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለስራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አከባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሳለቸው ታውቋል። ይህንን ተከትሎ ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የአይን እማኞች አስረድተዋል።  

ኮሚሽኑ ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ሪፖርት ከእነዚህ በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ስር የዋሉ  የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16  ሰዎች  ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ ሰዎች በጥይት ተመተው ስለተገደሉበት ሁኔታ ያስረዳል፡፡ 

በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ በዝርዝር እንደተመለከተው በዚሁ ሁኔታ የከረዩ አባገዳ ከዲር ሀዋስን ጨምሮ ኦዳ ጫርጨር፣ ቦሩ ፈንታሌ፣ ፈንታሌ ቦሩ፣ ቁምቢ ጉራቻ (ቃሉ ናቸው) ፣ ቦሩ ፈንታሌ፣ ቡላ ፈንታሌ፣ ሮባ ሀዋስ፣ ቦሩ ጎዳና፣ ጂሎ ደዲኦ፣ ቡላ ፈንታሌ፣ ቡልጋ ቦረኡ፣ ጂሎ ዲዶ እና ቦሩ ጂሎ የተባሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተመተው መገደላቸውንና 2 ሰዎች ደግሞ ወደ ጫካ በመሮጥ ማምለጣቸውን ምስክሮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

የሟቾችን አስከሬን ለማንሳት ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የሄዱ ሰዎች በቦታው በነበሩ ፖሊሶች እንዳያነሱ በመከልከላቸው፣ አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ መቆየታቸውንና የፈነዱና በከፊል በዱር እንስሳ የተበሉ ጭምር እንደነበሩ አስከሬኖቹን ያነሱና የቀበሩ ሰዎች ገልጸዋል። እንዲሁም አስከሬኖቹ ከጀርባ በኩል ወገባቸውና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች የነበሩባቸው መሆኑን ያስረዳሉ።  

በእለቱ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱት 39 የጅላ አባላት መካከል 23ቱ ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጅሎ ቦረዩ የተባለ የጅላ አባል ሕይወቱ አልፎ አስክሬኑ በሞጆ ከተማ ከሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ለቤተሰብ ተሰጥቷል። በአስክሬኑ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስል እና የድብደባ ምልክቶች ይታዩ እንደነበረ አስክሬኑን የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። የተቀሩት በእሰር ላይ የነበሩ የጅላ አባላት ከሳምንታት በኋላ ከእስር ተለቀዋል። 

ኢሰመኮ በምርመራው በሰበሰባቸውና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም.  በመንግስት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደውና የፀጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት፣ ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመተው የተገደሉ መሆኑንና ይህም ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ (extra judicial killing) ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ (reasonable ground to believe) ሆኖ አግኝቶታል። በተጨማሪም፣ በግዳጅ ከተወሰዱት 23 የጅላ አባላት መካከል አንድ ሰው ሞጆ ከተማ በሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ አልፎ  ያለምንም ምርመራ አስክሬኑን ቤተሰቦቹ እንዲወስዱና እንዲቀበር መደረጉ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ (extra judicial killing) መኖሩን በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ (reasonable ground to believe) ሆኖ አግኝቶታል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎችን እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ አስታውሰው፣ “ስለ ጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሰረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል” ብለዋል።

ሙሉ ሪፖርቱ ተያይዟል፦ “በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ የተደረገ የምርመራ ሪፖርት