የኢትዮጵያ ሰብአዊ መቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በሰላም ግንባታ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ሚናን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በጅማ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ እና ጉባዔው በጋራ ሊሠሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ጭምር የተደረገ ሲሆን፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ፕሬዝደንት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዲሁም የኢሰመኮ እና የጉባዔው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በመርኃ ግብሩ የሃይማኖት ተቋማት በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በሰላም ግንባታ ረገድ ያላቸውን ሚና እና የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን አስመልክቶ ለውይይት መነሻ የሚሆን ገለጻ ተደርጓል። በዚህም የሃይማኖት ተቋማት ግጭቶች ከመከሰታቸው አስቀድሞ በመከላከል ሂደት፣ ግጭቶችን በምክክር በመፍታት፣ በግጭት ምክንያት የተቋረጡ ግንኙነቶችን ወደነበሩበት በመመለስ እንዲሁም ተጎጂዎች ለጉዳታቸው ዕውቅና፣ ይቅርታ እና ካሳ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተብራርቷል። ‘ሳንታጂዲዮ’ (Sant’Egidio) የተሰኘ በሮም የሚገኝ የካቶሊክ እምነት ተቋም ሞዛምቢክን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ግጭቶችን የፈታበት ሂደት እንዲሁም የሴራሊዮን የሃይማኖት ተቋማት ለማኅበራዊ ፍትሕ መረጋገጥ ያላቸውን እምነት በመጠቀም በሀገሪቱ ተከባብረው ይኖሩ በነበሩ ሕዝቦች መካከል ለተፈጠረ ግጭት እልባት የሰጡበት አሠራር በተሞክሮነት ተጠቅሰዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሥራ ውጤቶች፣ ተግዳሮቶች እና የትብብር መስኮች ላይ አጭር ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ ኢሰመኮ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ለሃይማኖት ተቋማት ጉባዔው ምሥረታ ሲያደረግ የነበረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና ትብብር በጉልህ ተነስቷል። ቀደም ባለው ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ጅማ አካባቢ የተከሰተን ግጭት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት እና የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት በጋራ በመሆን የማረጋጋት ሥራ ማከናወናቸው እና የተቋማቱን የሃይማኖት መሪነት እና የሕዝብ አገልጋይነት ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ውጤታማ ተግባር ለመፈጸም ያስቻላቸውን ትብብር ተቋማዊ ማድረግ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ዕድል እንደሚሰጥ በመታመኑ “የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ምክክር የጋራ ጉባዔ” በሚል በ2003 ዓ.ም. እንደተቋቋመ ተገልጿል። ጉባዔው ለሀገር ሰላም ግንባታ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ያለውን አስተዋጽዖ ከግንዛቤ በማስገባት የሃይማኖት ተቋማት በ2007 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ መሪዎች ባደረጉት ውይይት አማካኝነት “የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ” ተብሎ ወደ ሀገር አቀፍ ተቋምነት ማደጉ ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሁለቱ ተቋማት ተባብሮ መሥራት ከዚህ ቀደም የነበረውን የእርስ በርስ ድጋፍ በማስቀጠል እና ለሰው ልጅ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ሁሉ በትብብር ለመሥራት በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያስችል አንስተዋል።



ውይይቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት “የጅማ ስምምነት” ተፈራርመዋል። ስምምነቱን በኢሰመኮ በኩል ዋና ኮሚሽነር ብርሀኑ አዴሎ፣ በጉባዔው በኩል ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የፈረሙ ሲሆን፣ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራትን በመለየት ስምምነቱን ለመተግበር የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚያከናውን ቡድን ተቋቁሞ ከሁለቱ ተቋማት ተወካዮች መካከል አባላት ተሰይመዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ፕሬዝደንት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ሰላም ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር አዳጋች መሆኑን በማንሳት፣ የሃይማኖት ተቋማት የሰዎች ባሕርይ እና ሥነ-ምግባር ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ የሚሠሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ ስምምነቱ ማኅበረሰባዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን በትብብር ለማከናወን እንደሚረዳ አስረድተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ሰብአዊ መብቶች በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ውስጥ በአንድም በሌላም መንገድ በግልጽ የተቀመጡ መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል። ውይይቱ በጅማ የተካሄደው አካባቢውና ኢሰመኮ ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምሥረታ እንዲሁም መልካም ውጤት ባስገኙ ተግባራት ውስጥ የነበራቸውን ሚና ለማስታወስና ዕውቅና ለመስጠት እንደሆነ አስገንዝበዋል። አክለውም በሰላም ግንባታ እና በተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች መብቶች ላይ በማተኮር በሚከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ ኢሰመኮ የግንዛቤና ክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን፣ የውይይት መድረኮችን እና የድጋፍ አማራጮችን በማመቻቸት ረገድ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።