“እኩልነት፡ ልዩነትን በማስወገድ ሰብአዊ መብቶችን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል የሚታሰበውን 73ኛውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) እንዲሁም ከሌሎች የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብሩ ቆይተዋል። 

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በጋራ የሚያከብሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ጽ/ቤት (OHCHR- EARO)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) እና አምስት አባላቶቹ በ2014 ዓ.ም. እንዲሁ በተመሳሳይ ትብብር የሰብአዊ መብቶች ቀናትን አክብረዋል። የኢሰመድህ አምስት አባል ድርጅቶች፣ ማለትም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA)፣ ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዲሞከራሲ (ቪኢኮድ /  (VECOD)፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል፣ ሴንተር ፎር ጀስቲስ (Centre for Justice)፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ማኅበር ከኅዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በዋና ዋና የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄዎችና ዝግጅቶች አካሂደዋል።

በታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ሁሉም ተባባሪ ድርጅቶች በጋራ ጊዮን ሆቴል በሚገኘው ጋርደን ግሩቭ ዎክ መናፈሻ የጋራ ዝግጅት ላይ የዚህን ዓመት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ-ቃል ዋና መልዕክት በማስተዋወቅ የዝግጅቶቹን መዝጊያ መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል። 

በእለቱ ድርጅቶቹ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን የሚያስተዋውቅ ባሕልና እሴት ላላቸው ማኅበረሰቦች ዕውቅና ሰጥተዋል። በዚህም መሰረት እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አንዱ ነበር (ተጨማሪ ለማንበብ)። 

በመዝጊያ መርኃ ግብሩ አጫጭር ፊልሞች የታዩ ሲሆን ፊልሞቹን መነሻ በማድረግ በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል። በተለይም የፊልም ፌስቲቫሉን በማዘጋጀት የተባበሩት የመዓዛ ፊልም ፕሮዳክሽን ማናጀር ወ/ሮ መዓዛ ወርቁ፣ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉ  በሀዋሳ እና በአዳማ ከተሞች ተካሂዶ እንደነበር ገልጸው፣ ይህ የመጀመሪያው ዙር ፌስቲቫል በአጭር ጊዜ ውስጥ የተካሄደ ቢሆንም የፌስቲቫሉን ዓላማ ለማስተዋወቅ እና የኪነጥበብ ባለሞያዎች ከኢሰመኮ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር መልካም ጅማሮ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ይህ የመጀመሪያው ዙር ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፌስቲቫል በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ያደረጉትን የኪነጥበብ ባለሞያዎችና ሌሎች ድርጅቶች አመስግነው፣ ፌስቲቫሉ ዓመታዊ እንደመሆኑ መጠን የሰብአዊ መብቶችን ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶችን መልዕክቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ መድረክ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።