የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለጾታ እኩልነት” በሚል መሪ ቃል ታስቦ ይውላል። ቀኑን አስመልክቶ የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ባስተላለፉት መልእክት “ቴክኖሎጂ ሴቶች እና ልጃገረዶች በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ፣ መደበኛና መደበኛ ያልሆነ የትምህርትና የሥራ ዕድል የማግኘት፣ ፍትሕን የማግኘት፣ በጤና እና በሥነ ተዋልዶ መብቶች ተጠቃሚ የመሆን መብቶቻቸውን ለማስከበር፤ ተገቢና ወቅታዊ መረጃን የማግኘት እና ሌሎች መብቶቻቸውን የማወቅና የመረዳት እንዲሁም ሐሳባቸውን የመግለጽ ነጻነታቸው እንዲረጋገጥ ያስችላል” ብለዋል። ኮሚሽነር መስከረም አክለውም “ቴክኖሎጂ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለማከናወን፣ ለሴቶች መብቶች ለመሟገት እና ንቅናቄ ለመፍጠር፣ የመብት ጥሰቶችን ሪፖርት ለማድረግ፣ ውይይት እና እንቅስቃሴ ለመፍጠር ትልቅ መሣሪያ ሲሆን ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶችም ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚገኘውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ለማዘመን ይረዳል” ሲሉ አስረድተዋል።

እ.ኤ.አ. በ2016 የዘላቂ የልማት ግቦች ሲወጡ በተለይም ያላደጉ ሀገራት ምቹና ተደራሽ ቴክኖሎጂን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የጾታ እኩልነት እና የሴቶችን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የማስቻል ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል።

በመሆኑም ዛሬ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፤ የሴቶችን ምቹና ተደራሽ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በተናጠልም ሆነ በቅንጅት የሴቶችን ጾታ-ተኮር ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ቴክኖሎጂ በማዘጋጀት፣ ተደራሽነቱን በማረጋገጥ፣ ሴቶች የቴክኖሎጂ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማብቃት፣ በበይነ-መረብ ቴክኖሎጂ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በመከላከል እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በመዘርጋት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያስፈልጋል፡፡