የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የ10 ወር የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትሕ እና የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት የኮሚሽኑ የአምስት ዓመት የስትራቴጂ እቅድ የመጀመሪያ የትግበራ ዓመት እንደመሆኑ መጠን፣ ዋና ዋና ተግባራት ተብለው ከተለዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች ጎን ለጎን በርካታ የተቋም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሷል። በዚህ ረገድ የኮሚሽኑን አካላዊና ዲጂታል ተደራሽነት የማሻሻል፣ በሰፊ ጥናት ላይ የተመሰረተ አዲስ መዋቅር በመተግበር ተቋሙን በሰው ኃይል ማብቃት፣ የበጀት ነጻነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችንና ደንቦችን በመቅረጽና ለሥራው አስፈላጊ የሆነ ሃብት በማሰባሰብ የኮሚሽኑን የፋይናንስ አቅም የማሻሻልና እንዲሁም ከሌሎች አቻ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትም ሆነ ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የተዘረጉ የትብብር ሥራዎች በዝርዝር ቀርበዋል።
በተጨማሪም በኢሰመኮ ሪፖርት ከተጠቀሱ በክትትልና ምርመራ ሥራዎቹ ባለፉት 10 ወራት ከተከናወኑ ሥራዎች ውስጥ በተለይ ግጭት የተከሰተባቸው 65 ቦታዎችን መድረሱን፣ ባለፉት 3 ወራት ብቻ 450 ሺህ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ አስር ስደተኛ ካምፖች ላይ የክትትል ሥራ ማከናወኑን፣ በአምስት ክልሎች የሚገኙ 1.5 ሚልዮን ገደማ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚያስጠልሉ 47 ጊዜያዊ መጠለያዎች፣ ጣቢያዎችን እና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን መጎብኘቱን እና ሪፖርት እና ምክረ ሃሳቦችን እንደየአግባብነቱ በይፋዊ መግለጫ ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካሎች ማቅረቡ ተገልጿል።
ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች አያያዝን በተመለከተ፣ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 82 ማረሚያ ቤቶች እና በ270 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማከናወኑንም ከተጠቀሱት የክትትልና የምርመራ ሥራዎች መካከል ናቸው።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ኮሚሽኑ የተቋማዊ ግንባታን በተመለከተ ያከናወናቸውን ተግባራት ገለጻ ሲያደርጉ፣ ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሚመሩበትና “የፓሪስ መርሆዎች” ተብለው በሚታወቁት መስፈርቶች/መርሆች መሰረት የሚጠበቅበትን ሙሉ በሙሉ በማሟላቱ የደረጃ አንድ (A Status) እውቅና ያገኘው ባለፉት 10 ወራት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ወቅት ባከናወናቸው ተግባራት አማካኝነት የለያቸውንና ምክር ቤቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችንና ምክረ ሃሳቦችንም አቅርበዋል።
በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት እንዲሁም በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ከብሔር ማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የአስተዳደር አካባቢዎች ወሰን አልፎ አልፎም ከሃይማኖት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ወቅቶች በሚያገረሹ ግጭቶች ሳቢያ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ እጅግ በርካታ ሰዎች ለሞት፣ ለአካልና ለሥነልቡና ጉዳት፣ ለመፈናቀልና፣ ለንብረት ውድመት መዳረጋቸውን አስምረውበታል። በመሰረተ ልማቶች ላይ በደረሰ ውድመትም መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፣ ከፍተኛና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን፤ ይህን አይነት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስጋትም እንደቀጠለ አስታውሰው፤ በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልል ተስፋፍቶ የነበረው ጦርነት አሁን ላይ መብረዱና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻሉ ተስፋ ሰጪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ በፍላጎቱ መጠን የተሟላ እንዲሆን፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ፣ ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሄና ፍትሕ እንዲረጋገጥ ገና ብዙ እርምጃዎችና ሥራዎች እንደሚቀሩ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አስር ወራት በተለያዩ ወቅቶች ከሕግ ውጪ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም፣ የዘፈቀደና ከፍርድ ወይም ክስ በፊት ያለ የተራዘመ እስር፣ በጋዜጠኞችና በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ እስራት እና የአንዳንድ እስር ቦታዎች አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢነት እየጨመረ በመምጣቱ የምክር ቤቱን ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተገልጿል፡፡
በጦርነትና በግጭት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የተጎዱ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ከማቋቋም ጎን ለጎን ሀገራዊው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና የኑሮ ውድነት፤ እንዲሁም በልዩ ልዩ ማህበራዊና መንግስታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ የሚሰማው የሕዝብ ቅሬታ ለሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ አደጋና ስጋት በመሆኑ የቅርብ ክትትል የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውም ሪፖርት ተደርጓል።
ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በማጠቃለያቸው ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት፤ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ፣ በመጠየቅና በማስፈጸም፣ ለሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።