እ.ኤ.አ. በ2006 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንተር ኤጀንሲ ቋሚ ኮሚቴ (Inter-Agency Standing Committee) በተፈጥሮ አደጋዎች ኑሮዋቸው የሚነካ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል ለማብራራት በሰብአዊ መብቶች እና በተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ያተኮሩ የአሠራር መመሪያዎችን የያዘ ሰነድ አጽድቋል፡፡ ሰነዱ አግባብነት ካላቸው የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች፣ በሥራ ላይ ካሉ የሰብአዊ ድጋፍ አሰጣጥን የሚመለከቱ ደረጃዎች እና ፖሊሲዎች ላይ ተመርኩዞ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የሰንዳይ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ማዕቀፍ (the Sendai Framework for Disaster Risk Reduction 2015 – 2030) እንደ ማስፈጸሚያ ሰነድነት ያገለግላል፡፡
የሰንዳይ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ማዕቀፍ አዳዲስ ሃሳቦችን እንዲይዝ ተደርጎ በ187 አባል ሀገራት በ3ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ኮንፈረንስ እ.ኤ.አ. በ2015 ጸድቋል። ይህ ማዕቀፍ መንግሥታት በቀዳሚነት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ የመሥራት ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲገልጽ፣ ኃላፊነቱ በዋነኛነት መንግሥት ላይ የሚወድቅ ቢሆንም ሁሉም ሰዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራዎች ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ሰነዱ ሀገራት የተከሰቱ አደጋዎች ስጋቶችን ቅነሳ እና አዳዲስ ስጋቶች እንዳይከሰቱ መከላከል ላይ እና ተጎጂዎችን በማቋቋም ላይ አጽንዖት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ሌሎች መመሪያ መርሆዎችን ያስቀምጣል።
Photo credit: EU/ECHO/Anouk Delafortrie