የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል ጋር በመተባበር የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር እና የአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) አፈጻጸምን አስመልክቶ በአባል ሀገር መንግሥታት ለአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን (African Commission on Human and Peoples’ Rights) በሚቀርበው ወቅታዊ ዘገባ ዙሪያ አውደ ጥናት ከነሐሴ 17 እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. አዘጋጅቷል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር እና የአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል አፈጻጸምን አስመልክቶ ለአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ አለበት። አውደጥናቱ በመንግሥት መቅረብ የነበረባቸውን ሦስት ዘገባዎች እንዲሁም የአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል አፈጻጸምን በተመለከተ የመጀመሪያ ዘገባ (initial report) የማቅረብ ግዴታውን ለመወጣት እንዲችል ጥራት ያላቸውን ዘገባዎች በማዘጋጀትና በማቅረብ ረገድ እገዛ ለማድረግ ያለመ ነው።

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች

በዚህ አውደ ጥናት ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከኢሰመኮ፣ ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ መንግሥታት ባጸደቋቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ውስጥ የተካተቱ መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎችን እና በአፈጻጸም ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ በየጊዜው የአፈጻጸም ዘገባማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከአህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች አካላት ጋር ካላት ግንኙነት አንጻር ያሉ ክፍተቶችን በመጥቀስ ኮሚሽነር መስከረም ከአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች አካላት ጋር ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው ሲሉ አጽንዖ ሰጥተው ተናግረዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ

አውደጥናቱ የአፍሪካ ቻርተር እና የማፑቶ ፕሮቶኮል አፈጻጸምን አስመልክቶ የሚቀርቡ መንግሥታዊ ዘገባዎች አዘገጃጀትን የሚቃኙ መመሪያዎች ላይ በተሳታፊዎች ዘንድ ግንዛቤን የፈጠረ ሲሆን፤ ተሳታፊዎቹ ለመጀመሪያ ረቂቅ ዘገባ (zero draft report) ጠቃሚ መነሻ ግብአቶች እንዲያጠናቅሩና የመንግሥታዊ ዘገባ አቀራረብ ላይ ተጨባጭ ልምምድ እንዲያደርጉ አስችሏል። ልምምዱ የሲቪል ማኅበራት እና እንደ ኢሰመኮ ያሉ የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በመንግሥት የሰብአዊ መብቶች አፈጻጸም ዘገባዎች ዝግጅት ወቅት ሊኖራቸው የሚችለውን ወሳኝ ሚና ያሳየ ነበር።

በአውደ ጥናቱ መጨረሻ ላይ ኮሚሽነር መስከረም የተሳታፊዎችን ንቁ ​​ተሳትፎ አድንቀው መንግሥት የአፍሪካ ቻርተር አፈጻጸም ወቅታዊ ዘገባ እንዲሁም የማፑቶ ፕሮቶኮል አፈጻጸምን በተመለከተም የመጀመሪያ ዘገባ ዝግጅቱን በቶሎ እንደሚጀምር እና ከዘገባ ዝግጅቱ ጅማሬ አንስቶ ከሲቪል ማኅበራትና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር እንደሚመክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።