በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ታኅሣሥ 10 የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ የተጀመረው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ሦስተኛ ዙር ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል። የዘንድሮው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አሳሳቢ ተብለው በተለዩት በሕይወት የመኖር መብት እና በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት በማግኘት መብት ላይ ያተኮረ ነው።
ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ኪነ ጥበብ ሰብአዊ መብቶችን ለማስተማር እና ‘‘ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን” ማየት የሚለውን ራዕዩን ለማሳካት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ከግምት በማስገባት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሚከናወን ዓመታዊ ዝግጅት ነው፡፡ በተጨማሪም ለባህል መብቶች ተመሳሳይ ትኩረት እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚያስታውስም ነው።
የዘንድሮው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በርካታ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና ክስተቶች የሚታሰቡበት ቀን ጋር መገጣጠሙ ለየት ያደርገዋል። በዋነኝነት ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights) የጸደቀበትን 75ኛ ዓመት፣ በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል እና ቅጣት ስምምነት የጸደቀበት እና የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) 20ኛ ዓመት የሚታሰቡበት ነው።
በ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. በተካሄዱት የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች ከ15 በላይ እና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጭር እና ፊቸር ፊልሞች እና የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ ቀርበዋል። ዘንድሮም ከፊልም ሥራዎች በተጨማሪ በልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለተሠማሩ ባለሙያዎች ዕድል ለመስጠት፣ ለማበረታታት እና ለሰብአዊ መብቶች ሥራዎች ድምጽ ለመሆን በማለም የአጫጭር ፊልም እና የፎቶግራፍ ውድድርን ለመጀመሪያ ጊዜ አካቷል።
ውድድሩ ከመስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ ቆይቶ ከ160 በላይ ባለሙያዎች የኪነጥበብ ሥራቸውን ለኮሚሽኑ በመላክ ተወዳድረዋል። ትኩረቱን በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ላይ ያደረገው በፎቶግራፍ ውድድር ጀማሪዎች (አማተር) እና ባለሞያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የአጫጭር ፊልም ውድድሩ ደግሞ በሕይወት የመኖር መብት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በአንድ በኩል በተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) የተቀረጸ እና ከ9 ደቂቃዎች ያልበለጠ አጭር ፊልም ዘርፍ ጀማሪዎችንም ባለሞያዎችንም አወዳድሯል። በሌላ በኩል ባለሞያዎች ብቻ የተሳተፉበት ከ25 ደቂቃዎች ያልበለጡ ዘጋቢ እና ልብ ወለድ ይዘት ያላቸው ፊልሞች ለውድድር ቀርበዋል።
ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ዝግጅት የአጫጭር ፊልሞች እና የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት፦
በፎቶግራፍ ውድድሩ:-
1ኛ. እዮብ ፈንታው – ‘‘ሁለት ዓለም’’ በሚል ርዕስ፣
2ኛ. መዓዛ አያሌው – ‘‘ሰሚ ያጣ ጩኽት’’ በሚል ርዕስ፣ እና
3ኛ. መቅደላዊት አሰፋ – ‘‘ጎጆ’’ በሚል ርዕስ አሸናፊ ሆነዋል።
ጀማሪ ባለሙያዎች በተሳተፉበት አጫጭር ፊልም ዘርፍ ውድድር፤
1ኛ. አዲሱ ደመቀ – ‘‘ስለ ሕይወት’’ በሚል ርዕስ፣
2ኛ. ኪዳኔ ሀብታሙ – ‘‘እምኅልዎት’’ በሚል ርዕስ፣ እና
3ኛ. ማሩፍ እንደራሴ – ‘‘ሃንጋቱ’’ በሚል ርዕስ ያቀረቧቸው አጫጭር ፊልሞች ያሸነፉ ሲሆን፤
ባለሙያዎች በተሳተፉበት አጫጭር ፊልም ዘርፍ ውድድር ደግሞ፤
1ኛ. አህመድ አብዱ – ‘‘ለምን?’’ በሚል ርዕስ
2ኛ. ዓለምእሸት ታደሠ – ‘‘ታቡ’’ በሚል ርዕስ እና
3ኛ. በረከት ተስፋዬ – ‘‘ተስፋ’’ በሚል ርዕስ ያቀረቧቸው አጫጭር ፊልሞች አሸናፊ ሆነዋል።
በተመሳሳይ በዝግጅቱ በአጫጭር ፊልም እና በፎቶግራፍ ውድድሩ ተሳታፊ ለነበሩና እስከ 10ኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁ ባለሙያዎች ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን የተመረጡ ተሳታፊዎች ፎቶግራፎች በአውደርይ መልክ ለታዳሚዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
ዘንድሮ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) 20ኛ ዓመት መታሰቢያ በመሆኑ በአፍሪካውያን ሴቶች የተሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎች የዕለቱ ዝግጅት ዋና ማዕከል እንዲሆኑ በማለም በቤዛ ኃይሉ ተደርሶ፣ በቅድስት ይልማ ተቀናብሮ፣ ማኅደር አሰፋ በመሪ ተዋናይነት እና አዘጋጅነት (ፕሮዳክሽን) የተሳተፈችበት ‘‘ዶቃ’’ ፊልም ለዕይታ ቀርቧል።
በአዲስ አበባው ዝግጅት ላይ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው በፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና የውጪ ሀገራት ተወካዮች፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ተወዳዳሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል፡፡ ፌስቲቫሉ ከታኅሣሥ 3 እስከ ታኅሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ቀናት በአሶሳ፣ ባሕር ዳር፣ ጋምቤላ፣ ሃዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ ጅማ፣ መቀሌ እና ሰመራ ከተሞች ውሰጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተካሂዶ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን የዘንድሮ መታሰቢያ ዝግጅት እና የዓመታዊ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ይጠናቀቃል።
በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለሰብአዊ መብቶች ያለንን ቁርጠኝነት የምናድስበት ነው። ይህ ኃላፊነት ከመንግሥት ወይም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም ከሲቪክ ማኅበረሰቡ እና ከሚድያው ብቻ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ግለሰብ መብቱን እና ግዴታውን በሚገባ ተረድቶ፣ የሌሎች ሰዎችን መብቶች ለማክበር፣ እንዲሁም የሰዎች መብቶች እንዲከበሩ በዐቅሙ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያጸናበት ቀን ነው ብለዋል። አክለውም በውድድሩ የተሳተፉ ሁሉ ጊዜያቸውን፣ የፈጠራ ችሎታቸውን እና ዐቅማቸውን ለሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ድምጽ ለመሆን መምረጣቸው ለሰብአዊ መብቶች ሥራ አጋዥ እና አበረታች መሆኑን አስረድተዋል።