የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ5ተኛ ጊዜ በሚያካሂደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የሚቀርቡ አጫጭር ፊልሞች እና ፎቶግራፎች ውድድር እስከ ኅዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ መገለጹ ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም፣ ለተጨማሪ ሰዎች ዕድል መስጠት በማስፈለጉ እና በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎች የጀመሯቸውን ሥራዎች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎችን የማስገቢያ ጊዜው እስከ ኅዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ተራዝሟል። 

ቀለል ያሉ የቴክኒክ መስፈርቶች እንዲሁም አበረታች ሽልማቶችን ያካተተው ውድድሩ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚካሄድ ሲሆን ፍላጎቱ ያለው ማንኛውም ሰው እንዲሁም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሳተፉበት ነው።  

የፎቶግራፍ ውድድሩ ትምህርት መብት ላይ የሚያተኮር ሲሆን፣ የአጫጭር ፊልሞች (በጀማሪዎች እና ባለሙያዎች ምድብ) ነጻነት መብት ላይ ያተኮረ ነው። 

በየውድድር ዘርፉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማቶች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ለሁሉም ተሳታፊዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት ይሰጣል። 

ሽልማቶች 

ደረጃ የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎች የአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች – የጀማሪዎች (5-6 ደቂቃ) የአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች– ባለሙያዎች (10-15 ደቂቃ) 
አንደኛ 75 ሺህ  100 ሺህ 125 ሺህ  
ሁለተኛ 50 ሺህ  75 ሺህ 100 ሺህ  
ሦስተኛ 25 ሺህ  50 ሺህ 75 ሺህ 

ኢሰመኮ ወጣቶች እና ታዳጊዎች እንዲሁም የኪነጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎችን ጨምሮ በፎቶግራፍ እና በአጫጭር ፊልም ሥራዎች ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በውድድሩ እንዲሳተፉ እና ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል። 

——– 

የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ውድድሮች የተሳትፎ ቅጽ በሁለቱም ዘርፍች የተቀመጡ ውድድር የቴክኒክ መስፈርቶች  እና የውድድሩ አጠቃላይ መመሪያዎችና ደንቦች ይመልከቱ።