የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ውስጥ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ውስጥ ተፈጸመ የተባለውን የብዙ ሰዎች ግድያ ወንጀልና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማጣራት የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ ፈጣን ምርመራ አካሂዷል።
የምርመራ ቡድኑ ከኅዳር 5 እስከ ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጎንደር ከተማ ተዘዋውሮ በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎችና ቤተሰቦች፣ ከዓይን ምስክሮች፣ ከመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎች፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች እና በጉብኝቱ ጊዜ በስፍራው ከነበሩ የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ምንጮች መረጃዎች ሰብስቧል። እንዲሁም ሆስፒታሎችን ጎብኝቷል፤ በህክምና ላይ የሚገኙ ሰዎችን እና የሚመለከታቸው አካላትን አነጋግሯል።
ይህ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት የፈጣን ምርመራውን አብይ ግኝቶች እና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ እና ዋና ዋና ምክረ ሃሳቦችን በአጭሩ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ዝርዝር የምርመራ ሪፖርቱ ተጨማሪ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማጣራት ወደፊት ይወጣል።